የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ለሀገር በቀል የኢንዱስትሪ ውጤቶች ሰፊ የገበያ አማራጭ እየፈጠሩ ይገኛሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ለሀገር በቀል የኢንዱስትሪ ውጤቶች ሰፊ የገበያ አማራጭ እየፈጠሩ ይገኛሉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2018(ኢዜአ)፦የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች የሀገር በቀል የኢንዱስትሪ ምርቶችን በግብዓትነት በመጠቀም ሰፊ የገበያ አማራጭ እየፈጠሩ መሆኑን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ ገለጹ፡፡
በዚህም የመዲናዋ አምራች ኢንዱስትሪዎች በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አዲስ አበባን በሁሉም መስክ የተሟላ መሰረት ልማት የተጎናጸፈች ውብ፣ ጽዱና ለነዋሪዎች ምቹ ከተማ የመገንባት ሥራ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የመዲናዋ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች አዲስ አበባን በአጭር ጊዜ ማራኪ ገጽታ ያላበሱ ናቸው።
በአጭር ጊዜ ውስጥ በመዲናዋ በጥራትና ስፋት የተገነቡ የመሠረተ ልማት ሥራዎችም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የዕድገት ጉዞን በስማርት ሥርዓት የሚያሳልጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ በኮሪደር ልማት የተገነቡና የሚገነቡ የልማት ሥራዎችም በሁሉም መመዘኛ ቀጣዩ ትውልድ ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከተማ እንዲኖረው የማስቻል ወሳኝ ጉዞ መሆኑን ተናግረዋል።
በመዲናዋ የአካባቢ ጥበቃ፣ የወንዝ ዳርቻ፣ የመንገድ፣ የፍሳሽ ማስወገጃና የኃይል አቅርቦት የልማት ሥራ ግብዓትነት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችም ለኢንዱስትሪ መልካም ዕድል መፍጠራቸውን አንስተዋል።
የኮርደር ልማት ዘላቂነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራትም ለኢንዱስትሪ ምርታማነት ምቹ አጋጣሚ በመፍጠር በርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ ነው ብለዋል።
የኮሪደር ልማት ሥራው የሚጠቀማቸው የሀገር ውስጥ ምርት ግብዓቶችም የኢንዱስትሪ ተኪ ምርታማነት አቅምን በማጎልበት የገበያ ትስስርና አማራጮችን እያሰፋ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተኪ ምርት ተነሳሽነት የሀገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባህል በማሳደግ የመዲናዋን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡ ማራኪ የልማት ሥራዎች የመዲናዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በማሳደግ ለኑሮና ቱሪስት መዳረሻነት ምቹ ከባቢ እየፈጠሩ ይገኛል።