በዞኑ ከ12 ሺህ 600 ቶን በላይ የማር ምርት ለገበያ ይቀርባል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ከ12 ሺህ 600 ቶን በላይ የማር ምርት ለገበያ ይቀርባል
ነቀምቴ ፤ ጥር 1/2018(ኢዜአ)፦ በምስራቅ ወለጋ ዞን በበጀት ዓመቱ 12 ሺህ 674 ቶን የማር ምርት ለገበያ እንደሚቀርብ የዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት አስታወቀ።
በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የልማት ኢንሼቲቭ ተቀርጾላቸው በአዲስ መልክ እየተሰራባቸው ካሉ የግብርና ስራዎች መካከል የማር ልማት አንዱ ነው።
የምስራቅ ወለጋ ዞን ለማር ልማት አመቺ ከሚባሉት የክልሉ ዞኖች አንዱ ነው።
በዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የእንስሳት እንክብካቤና ልማት ክፍል ሃላፊ አቶ አዲሱ ዳቤ፣ በዞኑ የሚገኘውን ምቹ የአየር ሁኔታ እና የደን ሀብት በመጠቀም የማር ምርት መጠንን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም 12 ሺህ 674 ቶን ለገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አንስተው በእስካሁኑ እንቅስቃሴ ከ8 ሺህ ቶን በላይ የማር ምርት ለገበያ መቅረቡን ገልጸዋል።
በዘርፉ የተያዘው እቅድ እንዲሳካም ዘመናዊ ቀፎዎች ለአርሶ አደሩ በስፋት እንዲቀርቡ መደረጉንም ነው የገለጹት።
በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ 2 ሺህ 500 ዘመናዊ ቀፎዎች ለአርሶ አደሩ የቀረበ ሲሆን በድምሩ በ38 ሺህ 147 ተሸጋጋሪ ቀፎ እና በ84 ሺህ 961 ባህላዊ ቀፎዎች የንብ ማነብ ስራው እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ከ26 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በንብ ማነብ ስራ መሰማራታቸውን ገልጸው አብዛኞቹ ማር አምራቾች በዞኑ ዲጋ ወረዳ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
የዲጋ ወረዳ የግብርና ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ይስሐቅ አዲሱ፣ በወረዳው በ22 ሺህ 500 ዘመናዊ ቀፎ የንብ ማነብ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 820 ቶን ማር ተመርቶ ለገበያ መቅረቡን አንስተው በወረዳው 13 ሺህ 760 አርሶ አደሮች በንብ ማነብ ስራው ተሰማርተው ይገኛሉ ብለዋል።
በማህበር ከተደራጁ ማር አምራች የወረዳው አርሶ አደሮች መካከል ማሞ ኡመታ እና ጓደኞቻቸው ሰባት ሆነው በ50 ዘመናዊ ቀፎ የንብ ማነብ ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ።
ባለፈው ዓመት 120 ኪሎ ግራም ለገበያ ማቅረባቸውን ተናግረው በዚህ ዓመት 200 ኪሎ ግራም ማር ለገበያ ለማቅረብ እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛው የወረዳው ነዋሪ አቶ ብርሃኑ ሂንኮ፤ ባላቸው ሰባት ዘመናዊ ቀፎ የንብ ማነብ ስራ እያከናወኑ ሲሆን ዘንድሮም 40 ኪሎ ግራም ማር ለገበያ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።