በንጋት ሰው ሰራሽ ሐይቅ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ አልሚዎች ምቹ የልማት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል - ኢዜአ አማርኛ
በንጋት ሰው ሰራሽ ሐይቅ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ አልሚዎች ምቹ የልማት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል
አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2018(ኢዜአ)፦በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የንጋት ሰው ሰራሽ ሐይቅ ላይ በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ አልሚዎች ምቹ የልማት ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።
የለውጡ መንግስት ቱሪዝምን ከአምስቱ ግንባር ቀደም የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል በማድረግ ለቅርስ ጥበቃ፣ ዕድሳትና ለአዳዲስ የመዳረሻ ልማት የሰጠው ትኩረት ዘርፉ እንዲያንሰራራ አስችሏል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በርካታ ቀልብን የሚስቡ ታሪካዊ፣ ኃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ የመስህብ ዕምቅ ጸጋዎችን የታደለች ሀገር ናት።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህም የኢትዮጵያን ዕምቅ የመስህብ ጸጋዎች በመንከባከብና በማልማት የቱሪዝም ሃብት ወሳኝ የኢኮኖሚ አቅም እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተገነቡ ማራኪ የመዳረሻ ሥፍራዎችም ለጎብኝዎች ምቹ ምኅዳርን በመፍጠር የቱሪዝም ተወዳዳሪነትን በእጅጉ እያሳደጉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቱሪዝም፣ የዓሳ ሃብት ልማት፣ የውሃ ላይ ትራንስፖርትና መሰል የመስህብ መዳረሻ ኢንቨስትመንትን ማሳደግ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱንም አስረድተዋል።
በሕዳሴ ግድብ የንጋት ሐይቅ እና ዙሪያውን ለማልማት የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ የግሉን ዘርፍ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ተሳትፎ የሚያሳድግ ዕድል መፍጠር እንደቻለ ገልጸዋል።
ለዚህም የግሉ ዘርፍ በንጋት ሐይቅ የቱሪዝም ልማት ኢንቨስትመንት ተሳትፎን ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት፣ ከፌደራልና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መንግስት ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በንጋት ሐይቅ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ለሚሳተፉ አልሚዎችም የግንባታ መሳሪያ፣ ተሽከርካሪ እና መሰል ቁሳቁሶች ከቀረጥ ነፃ አገልግሎት የሚያገኙበት ዕድል መመቻቸቱን አስታውቀዋል።