የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በየዘርፉ ለሚዘጋጁ እቅዶች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ትክክለኛ ግብዓት ያስገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በየዘርፉ ለሚዘጋጁ እቅዶች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ትክክለኛ ግብዓት ያስገኛል
ሐረማያ፤ ጥር 1/2018(ኢዜአ)፦ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በየዘርፉ ለሚዘጋጁ እቅዶች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ትክክለኛ ግብዓት እንደሚያስገኝ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ገለጸ።
አገልግሎቱ ለሁለተኛ ዙር የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ የአሰልጣኞች ስልጠና በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ባለሙያዎች በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ እየሰጠ ነው።
በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከፍተኛ የስታቲስቲክስ ባለሙያ እና በስልጠናው የቴክኒክ ዋና አስተባባሪ ሃይሌ ዓለሙ እንዳሉት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዘርፈ ብዙና የተለያዩ መረጃዎችን ይሰበስባል፤ ይተነትናል።
የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ለሚያደርጉ ባለሙያዎችም የአሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው፤ በስልጠናው የኢኖሚ ድርጅቶች ትርጉም፣ ጽንሰ ሃሳብ፣ ዓላማና ሌሎች መረጃ ለመሰብሰብ የሚያገለግሉ ሃሳቦችን የሚገነዘቡበት መሆኑን ተናግረዋል።
የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ዓላማም የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሃብት ደረጃ ለማወቅና ድርጅቶችን በዓይነት፣ በብዛትና በደረጃ ለመለየት እንዲሁም ለጥናትና ምርምር፣ ለፖሊሲ፣ ለስትራቴጂና እቅድ ዝግጅት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት ብለዋል።
በአገልግሎቱ የሐረር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ሙክታር ጀማል እንደገለጹት በቅርንጫፉ አስተባባሪነት ከሐረር፣ ድሬዳዋ፣ ጭሮ፣ ጎዴና ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ለተውጣጡ 180 ሰዎች የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት ተጀምሯል።
የአሰልጣኞች ስልጠናው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥር 10 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚቆይ ጠቁመው፤ ስልጠናው ጥራትና ወቅቱን የጠበቀ፣ ተገቢነትና ተአማኒነት ያለው መረጃ መሰብሰብ የሚያስችል ክህሎት እንዲያገኙና ሌሎችን እንዲያበቁ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።