በክልሉ በጤና ተቋማት ወቅቱን የተከተለ የዲጂታል አሰራርን በመተግበር የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በጤና ተቋማት ወቅቱን የተከተለ የዲጂታል አሰራርን በመተግበር የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ ትኩረት ተደርጓል
ሰመራ፤ ጥር 1/2018(ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል በጤና ተቋማት ወቅቱን የተከተለ የዲጂታል አሰራርን በመተግበር የእናቶችን ጤና ለመጠበቅ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለፀ።
ቢሮው "ፈጠራና ዘላቂ ፋይናንስ ለእናቶች ጤና" በሚል መሪ ሐሳብ ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣይ አንድ ወር በተለያዩ ኹነቶች የሚከበረውን የእናቶች ጤና ወርን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዊቲካ ኖሬ በመግለጫቸው እንዳሉት የእናቶችን ጤና መጠበቅ ሲቻል የቤተሰብና የህብረተሰብ ጤና የተጠበቀና ጤናማ ትውልድ ማፍራት ያስችላል።
በዚህም በቀጣይ በሚከናወኑ ኹነቶች ፈጠራና ክህሎትን በማሳደግ እንዲሁም በጤና ተቋማት የማዋለጃ ቁሳቁሶችን ማዘመንና ወቅቱን የተከተለ የዲጂታል አሰራር ላይ ትኩረት በማድረግ ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።
ዘላቂነት ያለው የገንዘብ ምንጮችን በማጎልበት በእናቶች ደህንነት እና ጤና ላይ ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራም አስረድተዋል።
በተለይም አቅመ ደካማ እናቶችን በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ከባለሃብቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመስራትና በአካባቢ ያለን ፀጋ በመጠቀም የገንዘብ ማግኛ አማራጮችን የማስፋት ስራም ይሰራል ብለዋል።
በዚሁ በእናቶች ወር ከሚከናወኑት የንቅናቄ ስራዎች መካከል በተለይም የአርብቶ አደሩ አካባቢ እናቶች በጤና ተቋማት ብቻ እንዲወልዱና የህክምና ክትትላቸውን እንዲያደርጉ ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከተንቀሳቃሽነት የኑሮ ዘይቤ ይልቅ በቋሚ ስፍራ እንዲኖሩ የሚያስችሉ ተግባራትም በትኩረት ይከናወናሉ ብለዋል።
በክልሉ የጤና ክትትል የሚደረግላትና ደህንነቷ የተጠበቀ እናት እንድትኖር የሚከናወኑ ተግባራት እንዲጠናከሩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
በቅርቡ የተከፈተው የዱብቲ የእናቶችና ህፃናት ህክምና ማዕከልን እንደ አብነት ያነሱት ምክትል ሃላፊው፤ መሰል የጤና ተቋማትን ማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራበት መሆኑን ገልፀዋል።
በእናቶች ጤንነትና ደህንነት ላይ የሚሰሩ ስራዎች መመዝገብ፣ መከታተልና ማስቀመጥ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚከናወንም ነው ያስረዱት።