በክልሉ በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሬትን በተፈጥሮ ማዳበሪያና በኖራ በማከም ወደ ምርት ለማስገባት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሬትን በተፈጥሮ ማዳበሪያና በኖራ በማከም ወደ ምርት ለማስገባት እየተሰራ ነው
አዳማ፤ ጥር 1/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሬትን በተፈጥሮ ማዳበሪያና በኖራ በማከም ወደ ምርት ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለፀ።
በቢሮው የአፈር ለምነት ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ እሸቱ ለገሰ ለኢዜአ እንደገለጹት የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የአፈር ለምነትና ጤንነት የመጠበቅ ስራ ትኩረት አግኝቷል።
በተለይም በአሲድ የተጠቃ መሬትን በተፈጥሮ ማዳበሪያና በኖራ ለማከም ለአርሶ አደሩ ግንዛቤና ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በክልሉ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለአፈር አሲዳማነት ተጋላጭ መሆኑን አንስተው ችግሩን ለመቅረፍም መሬቱን በተፈጥሮ ማዳበሪያና በኖራ ለማከም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያውም በኮምፖስትና በቨርሚ ኮምፖስት እንዲሁም የባዮ ጋዝ ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ በእስካሁኑ ሂደትም ከ100 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቶ አገልግሎት ላይ እየዋለ ይገኛል ብለዋል።
የኖራ አቅርቦትን ለማሳደግም በጉደር የኖራ ፋብሪካ በቀን 800 ኩንታል ኖራ የመፍጨት አቅም ያላቸው ሁለት ወፍጮዎችን የመትከል ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
የምዕራብ አርሲ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት የአፈር ለምነት ቡድን መሪ አቶ አብደላ ኢብራሂም እንደገለጹት በዞኑ 100 ሺህ ሄክታር የሚሆን መሬት በአፈር አሲዳማነት መጠቃቱን ተናግረዋል።
መሬቱን ወደ ለምነት ለመመለስም ባለፈው ዓመት 25 ሺህ ኩንታል ኖራ ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት በአሲዳማነት የተጠቃውን መሬት የማከም ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
ከኖራ አቅርቦቱ በተጓዳኝ በተፈጥሮ ማዳበሪያ መሬቱን በማከም ምርታማነትን የመጨመር ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በዞን ደረጃ ከ13 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።