ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ የተወሰዱ የፖሊሲ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት አስገኝተዋል

አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ የተወሰዱ የፖሊሲ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት ማምጣታቸውን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

ሚኒስትሯ በጥር ወር የሚከበረውን "የጤናማ እናትነት ወር" አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ባለፉት ዓመታት ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት የጤና ችግርና ሞትን ለመቀነስ በተደረገው ርብርብ በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ቁጥር መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

በጤና ጣቢያዎች የቀዶ ሕክምና አገልግሎት መጀመሩ ለውጥ ማምጣቱንም ጠቅሰው የጤና ተቋማት ተደራሽነት መስፋት የቅድመ ወሊድ ክትትልን ማሳደጉንም ነው የገለጹት፡፡

ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የደም መፍሰስን በመከላከል በኩል የበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ሚና እና ቁጥር ማደጉንም ተናግረዋል፡፡

እስካሁን የተገኙ ውጤቶች አበረታች መሆናቸውን ጠቁመው በቀጣይም የተሻሉ ውጤታማ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል፡፡

ለዚህም ፈጠራ እና ዘላቂ ፋይናንስ ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰው የዲጂታል ጤና መረጃን ተደራሽ ማድረግ፣ የሕክምና ግብዓቶችን ማሟላትና የቀዶ ሕክምና አገልግሎትን ማስፋት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

ጤናማ እናትነት አንዲት ሴት በእርግዝና፣ በወሊድና በድህረ ወሊድ ወቅት የሚኖራት ሁለንተናዊ ጤንነት ነው።

የዘንድሮው የጤናማ እናትነት ወር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ39ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ ''ፈጠራና ዘላቂ ፋይናንስ ለጤናማ እናትነት'' በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶች ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም