በዞኑ ከ37 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ለምቷል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ከ37 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ለምቷል
ደብረ ማርቆስ፤ጥር 1/2018(ኢዜአ)፡-በምስራቅ ጎጃም ዞን ከ37 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ማልማት መቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።
በመምሪያው የመስኖ ልማት ቡድን መሪ አቶ ሃብታሙ አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ የመስኖ ልማቱን ምርታማነት በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል ርብርብ እየተደረገ ነው።
በበጀት ዓመቱም በ1ኛ ዙር ብቻ ከ41 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ከ37 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈን መቻሉን ገልጸዋል።
በመስኖ ከለማው መሬትም ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።
የበጋ መስኖ ልማት ስራው ከ120 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ከ9 ሺህ 700 በላይ የሞተር ፓምፕ እና ዘመናዊ የመስኖ ግንባታዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን አስረድተዋል።
የመስኖ ልማቱን ምርታማነት ለማሳደግም ከ84 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ መዋሉን ጠቁመዋል።
በመስኖ የለሙ አትክልትና ሰብሎችን ከተባይ የመከላከልና የመንከባከብ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በዞኑ በመስኖ ልማት ስራው ከተሰማሩ አርሶ አደሮች መካከል የጎዛምን ወረዳ የመጣያ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር መኩሪያው የስጋት እንዳሉት የዝናብ ወቅትን ብቻ ጠብቀው በማምረት ቤተሰባቸውን በተገቢው ማስተዳደር እንዳልቻሉ አስታውሰዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በመስኖ ልማት በመሰማራት በዓመት ሁለት ጊዜ በማምረት የቤተሰባቸውን የምግብ ዋስትና እንዳረጋገጡ ጠቁመዋል።
በመስኖ ስንዴንና የጓሮ አትክልቶችን በማልማት በዓመት እስከ 90 ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ እንደሚያገኙም ተናግረዋል።
የዚሁ ወረዳ የደሳ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ያለምወረቅ ምህረት በበኩላቸው ባለፈው ዓመት በመስኖ የጓሮ አትክልት በማልማት ከ30 ሺህ ብር በላይ ተጨማሪ ገቢ ማግኘታቸውን አውስተዋል።
በያዝነው በጋ የምርት ማሳደጊያ ግብዓት በመጠቀማቸው ምርታማነታቸውን በማሳደግ ከ40 ሺህ ብር በላይ ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።
በዞኑ ባለፈው ዓመት በ1ኛና 2ኛ ዙር በመስኖ ከለማው መሬት ላይ አራት ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት መገኘቱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።