ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ህጋዊ መብትን መሰረት ያደረገ የሀገር ህልውና ጉዳይ እና የትውልድ ጥያቄ ነው 

ሀዋሳ፤ ጥር 1/2018(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ህጋዊ መብትን መሰረት ያደረገ የሀገር ህልውና ጉዳይ እና የትውልድ ጥያቄ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከሀገር ህልውና እና የኢኮኖሚ እድገት ጋር በቀጥታ የተያያዘ በመሆኑ ምላሽ የሚሻ የትውልድ ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ በተለይም በግብርና እና በኢንዱስትሪ ምርቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በምታደርገው ጥረት  የተቀላጠፈ የሎጂስቲክስ አገልግሎት የሚኖራትም የራሷ የባህር በር ሲኖራት መሆኑ ይታመናል።

ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም በአካባቢው የጂኦ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን አጠናክራ ለመቀጠልና ብሔራዊ ደህንነትን ለማስጠበቅ የራሷ የባህር መግቢያና መውጫ ያስፈልጋታል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ አህጉራዊ የምጣኔ ሃብት ትስስርን ከማጠናከር ባለፈ የሀገርን ሉዓላዊነት የማስከበርና የባህር ላይ ስጋቶችን የመከላከል ጉዳይ መሆኑም እርግጥ ነው።

በመሆኑም የምጣኔ ሃብት፣ የፖለቲካ፣ ዲፕሎማሲያዊና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮች ታክለውበት የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የህልውና ጉዳይ መሆኑን የሚያረጋግጡ ምክንያቶች ናቸው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢዜአ ያነጋገራቸው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የህጋዊነትና ተፈጥሯዊ መብት እንዲሁም የትውልድ አደራና የሀገር ህልውና ጥያቄ መሆኑን አንስተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ በዓሉ ጡቄላ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ እና ቀይ ባህር ሊነጣጠሉ የማይችሉ ተፈጥሮ ያቆራኘቻቸውና የታሪክ እውነታ ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የምጣኔ ሃብት ጉዳይ፣ የብሔራዊ ደህንነትና አጠቃላይ የሀገር ህልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጸው ምላሽ የሚሻ የትውልድ ጥያቄ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በድምሩ የሀገር ህልውና ጉዳይ በመሆኑ ምላሽ እስኪያገኝ የሁላችንም ጥረትና ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

በዩኒቨሲርቲው የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ጌታቸው አየለ(ዶ/ር)፤ በታሪክም፣ በመልክአ ምድርም ይሁን በዓለም አቀፍ ህግ ኢትዮጵያን ከቀይ ባሀር ነጥሎ ማየት አይቻልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን ከራሷ ባለፈ አህጉራዊ የምጣኔ ሃብት ትስስርን እንደሚያጠናክርም አስረድተዋል።

በመሆኑም ጥያቄው በዓለም አቀፍ ህግ፣ በታሪክም ይሁን በመልክዓ ምድር አሳማኝ ምክንያቶች ያሉት በመሆኑ ተገቢ ምላሽ እንዲያገኝ የሁላችንም ጥረት መቀጠል አለበት ብለዋል።  

የኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰነውና የትውልዱ ጥያቄ ሆኖ እየተነሳ ያለው የባህር በር ጥያቄ ፈጣን ምላሽ የሚሻ መሆኑንም አስገንዝበዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም