ኢትዮጵያ በኮሪደር ልማትና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለዓለም ተምሳሌት የሚሆን ተግባር ፈፅማለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በኮሪደር ልማትና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለዓለም ተምሳሌት የሚሆን ተግባር ፈፅማለች
አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በኮሪደር ልማትና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለዓለም ተምሳሌት የሚሆን የላቀ ውጤት እያስመዘገበች ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ ገለፁ።
በኢትዮጵያ ከተሞችን ለነዋሪዎች እና ለኢንቨስትመንት ምቹ የሚያደርጉ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በርካታ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በኮሪደር ልማት ከተሞችን ውብና ለኑሮ ምቹ ከማድረግ በተጨማሪ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምና አረንጓዴ ኢኮኖሚን መገንባት የሚያስችሉ ውጤታማ ስራዎችም ተከናውነዋል።
በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ራይ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ የጠንካራ ዕቅድና አፈፃፀም እንዲሁም የላቀ የአመራር ብቃት ማሳያ ነው።
በተለይም በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ውብና ማራኪ ገፅታ ያላበሰ ነው ብለዋል።
ይህም በኢትዮጵያ ለመኖርና ሀብት ማፍራት ለሚሹ የውጭ ዜጎችም ምቹ መደላድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረውና ለተከታታይ ዓመታት የተተገበረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርም ኢትዮጵያ ተምሳሌት የሆነ ስኬታማ ተግባር ማከናወኗን አምባሳደሩ ገልፀዋል።
በዚህ ታላቅ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ በጥቂት አመታት ውስጥ ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኝ በመትከል ዓለምን ያስደመመ ተግባር ያከናወነችበት ነው።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በመላ ሀገሪቱ የአረንጓዴ ስፍራዎች እንዲበራከቱ ማድረጉን አንስተው በዚህም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እውቅና እንድታገኝ አስችሏል ብለዋል።