ለጥምቀት በዓል ወደ ጎንደር ከተማ የሚመጡ የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ፓርኩን እንዲጎበኙ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ለጥምቀት በዓል ወደ ጎንደር ከተማ የሚመጡ የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ፓርኩን እንዲጎበኙ ዝግጅት ተደርጓል
ጎንደር፤ ጥር 1/2018 (ኢዜአ)፡-የጥምቀት በዓልን ለማክበር ወደ ጎንደር ከተማ የሚመጡ የውጪ ሀገር ቱሪስቶች የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን እንዲጎበኙ ልዩ የጉብኝት ፓኬጅ መዘጋጀቱን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የፓርኩ ጽህፈት ቤት ተወካይ ሃላፊ አቶ ላቀው መልካሙ ለኢዜአ እንደገለጹት የጥምቀት በዓልን ለመታደም ወደ ጎንደር ከተማ የሚመጡ የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ፓርኩን እንዲጎበኙ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል፡፡
የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ዋልያ፤ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮን ጨምሮ ሌሎች ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አዕዋፋት መገኛ ስፍራ በመሆኑ በጎብኚዎች ተመራጭ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህን የሀገር ቅርስ ጥምቀትን ምክንያት በማድረግ ለማስጎብኘት መታቀዱን የገለጹት አቶ ላቀው፣ የጉብኝት ፓኬጁ ተራራ መውጣት፤ የእግር ጉዞዎች፤ ብርቅዬ የዱር አንስሳት የሚገኙባቸው ስፍራዎችን መጎብኘት እንደሚያካትት ተናግረዋል።
የፓርኩን መሰረተ ልማቶች የመጠገንና የማስተካከል ሥራዎች መከናወናቸው ጠቁመው፣ ፓኬጁ መዘጋጀቱ የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ያስችላል ብለዋል።
ለቱሪስቶች ማረፊያ የሚያገለግሉ የካምፕና የድንኳን መጠለያ ቦታዎችን፣ የውሃ ተቋማትንና መጸዳጃ ቤቶችን በማዘጋጃት የተሟላ መስተንግዶ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
በአካባቢው በአስጎብኝነትና በምግብ አብሳይነት የተደራጁ ማህበራትን በቅድመ ዝግጅት ወቅት በቱሪስቶች መስተንግዶና አያያዝ ስልጠና መሰጠቱንም አስረድተዋል፡፡
የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ቁጥርን ለማሳዳግ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ ፓርኩን የማስተዋወቅ ሥራዎች በስፋት መከናወናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ላቀው ገለጻ ባለፉት ስድስት ወራት ፓርኩን የጎበኙ የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ቁጥር 1ሺህ 400 መድረሱን ጠቁመው፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ600 እድገት አሳይቷል ብለዋል
የደባርቅ የኢኮ ቱሪዝም ማህበራት ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ ቄስ ሞገስ አየነው በበኩላቸው የፓርኩ የቱሪስት ፍሰት መጨመር በዩኒየኑ የታቀፉ አባላት ከቱሪዝም ገቢው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል፡፡
ስምንት ሺህ የሚደርሱ የዩኒየኑ አባላት በቅሎ በማከራየት፣ የጎብኚዎችን እቃ በመጫን፣ በማጀብና መንገድ በመምራት ቱሪስቶችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1978 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም የተፈጥሮ ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡