አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት ነዋሪዎች መንግስታዊ አገልግሎቶችን በቅርበት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት ነዋሪዎች መንግስታዊ አገልግሎቶችን በቅርበት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል
ሮቤ ፤ጥር 1/2018 (ኢዜአ):-በኦሮሚያ ክልል ተግባራዊ የተደረገው አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት መንግስታዊ አገልግሎቶችን በቅርበት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን በባሌ ዞን የሀረና ቡሉቅ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።
የዞኑ አስተዳደር በበኩሉ በ189 ቀበሌዎች የተዋቀረው አደረጃጀት ለነዋሪዎች አገልግሎት በቅርበት ለመስጠት ከማስቻሉ ባለፈ ጊዜና ወጪን በመቆጠብ በልማት ሥራዎች ላይ እንዲያተኩሩ ማድረጉን ገልጿል።
አዲሱን የቀበሌ አደረጃጀት በማስመልከት አስተያየታቸውን ከሰጡ የሀረና ቡሉቅ የቁምቢ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሀሰን አህመድ እንዳሉት፣ አደረጃጀቱ ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎቶች በቅርበት ለማግኘት አስችሏቸዋል።
ከዚህ በፊት መንግስታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ወደ ወረዳና ከተማ አስተዳደር የሚያደርጉት ምልልስ ጊዜና ድካም እንደነበረው አስታውሰው "አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት ይህንን በማቃለል ተጠቃሚ አድርጎናል" ብለዋል።
ሌላኛው ተገልጋይ አቶ አህመድ መሐመድ በበኩላቸው እንዳሉት የቀበሌ አደረጃጀቱ የህዝብን የልማት ተሳትፎ በማሳደግ ከዚህ በፊት የነበሩት የመሰረተ ልማት ችግሮች በህብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲፈቱ ዕድል ፈጥሯል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ከተከናወኑ የልማት ሥራዎች መካከል ድልድይና ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የሀረና ቡሉቅ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ሀሰን በበኩላቸው አዲሱ አደረጃጀት የወረዳውን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በቅርበት ለመመለስ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።
የባሌ ዞን አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ብርሃኑ አርፋሳ በበኩላቸው በዞኑ የሚገኙ 189 ቀበሌዎች በአዲሱ አደረጃጀት ተዋቅረው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግሯል።
በቀበሌ አደረጃጀቶችም አመራሮች ተመድበው ህብረተሰቡን በቅርበት እንዲያገለግሉ መደረጉን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ብርሀኑ ገለጻ በአዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት እየተሰጠ ያለው የህዝብ አገልግሎት ከዚህ በፊት ወደ ዞንና ወረዳዎች በተደጋጋሚ ይመጡ የነበሩ ቅሬታዎችን እየቀነሰና የህዝብ እርካታን እየጨመረ መጥቷል።
በቀበሌዎቹ የተመደቡ አመራሮችና በለሙያዎች ህብረተሰቡን በተሻለ እንዲያገለግሉ የአቅም ግንባታ ሥልጠናና የድጋፍና ክትትል ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በቅርበት ለመፍታት አዲስ የቀበሌ አደረጃጀት ተግባራዊ መደረጉ ይታወሳል።
አደረጃጀቱ ህዝቡ በልማት ተጠቃሚ እንዲሆንና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቹም በህዝብ ተሳትፎ መፍትሄ እንዲያገኙ ያለመ መሆኑ እንዲሁ።