የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ማረጋገጥ የትውልዱ ወሳኝ የቤት ሥራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ማረጋገጥ የትውልዱ ወሳኝ የቤት ሥራ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር1/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ከፍተኛ እና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያሳልጥ አስተማማኝ የባሕር በር ባለቤትነትን ማረጋገጥ የአሁኑ ትውልድ ወሳኝ የቤት ሥራ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።
በቀይ ባሕር ነባራዊ እውነታ ውስጥ ኢትዮጵያ የነበራትን ከፍተኛ ቦታ ያጣችው የህዝብ ውክልናን ችላ በማለት በተሰጠ የተሳሳተ ውሳኔ እና ሸፍጥ መሆኑ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ በተሸረበባት ታሪካዊ ሸፍጥ የባሕር በሯን በማጣቷ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በሌሎች ሀገራት ወደብ ላይ ጥገኛ እንድትሆን ተገዳለች፣ ይህ ደግሞ በኢኮኖሚ ዕድገቷና በሉዓላዊነቷ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል።
የተለያዩ ሀገራት፣ የታሪክ አዋቂዎች፣ ምሁራንና ህብረተሰቡ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር ምክንያታዊና ፍትሃዊ የስትራቴጂክ ጉዳይ መሆኑን ያነሳሉ።
የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የስልጣኔ ኃያልነት ከቀይ ባሕርና ዓባይ ወንዝ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው።
የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶች በሸረቡት ሴራ ኢትዮጵያ ከስልጣኔዋ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ካለው አስተማማኝ የባሕር በሯ እንድትገለል መደረጉን አስታውሰዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዋጋ እንድትከፍል መገደዷን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያን ከፍተኛ የህዝብ ቁጥርና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያሳልጥ አስተማማኝ የባሕር በር ባለቤትነት ማረጋገጥ የአሁኑ ትውልድ ወሳኝ የቤት ሥራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር የፖሊሲና ስትራቴጂ ተመራማሪ ተመስገን ዋለልኝ(ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣት በሎጀስቲክስ እንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይና ትራንዚት ከምታወጣው ገንዘብ ባለፈ በወጪና ገቢ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ ዓለም አቀፍ የንግድ ተወዳዳሪነትን እያቀጨጨ መሆኑን ገልጸዋል።
የባሕር በር ባለቤትነትን ለማረጋገጥ የቀረበው ጥያቄ የሎጀስቲክስ ዘርፍ የኢኮኖሚ ስብራትን በዘላቂነት የሚጠግን ወሳኝ የዲፕሎማሲ አካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።