በምስራቅ ሸዋ ዞን ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ሸዋ ዞን ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ይካሄዳል
አዳማ፤ ጥር 1 /2018 (ኢዜአ)፡-.በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት እንደሚካሄድ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ባለፉት አመታት በሕዝብ ተሳትፎ የተከናወኑ የተቀናጁ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች ለተፈጥሮ ሀብት መጠበቅና የከርሰ ምድር ገጸምድር ውሀ ሀብቶች እንዲጎለብቱ አድርጓል።
እነዚህን ውጤቶች በማስፋትም በምስራቅ ሸዋ ዞን የተራቆቱ በስነ-አካላዊና ስነ- ህይወታዊ የተፋሰስ ልማት ስራዎች በማከናወን የአፈር ለምነትንና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም እያገዙ ናቸው።
የምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብነት ዘገየ ለኢዜአ እንዳሉት በየዓመቱ በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ተጨባጭ ለውጦች ታይተዋል።
ይህን ለማሳካትም የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና የከርሰ ምድርና ገጸ ምድር የውሀ መጠን መጨመር እንዳስቻሉ ጠቁመዋል።
በዞኑ ተግባሩን በማስቀጠልም በዘንድሮ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ 421 ሺህ 651 ሰዎች የሚሳተፉበት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
በዚህም በ270 ተፋሰሶችን ማዕከል በማድረግ 119 ሺህ 495 ሄክታር መሬት እንደሚለማ ተናግረዋል።
በዚህም እንቅሰቃሴ ሥነ-አካላዊና ሥነ-ህይወታዊ ስራ በመስራት የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ ትኩረት መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ይህም በመሬት መራቆት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እና የመሬት ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
እንዲሁም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የተጎሳቆለ መሬት ከሰውና እንስሳት በመከለል መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
የዘንድሮውን እቅድ ለማሳካት በየደረጃው በቅንጀት መስራትና በውጤት ማጀብ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማቱም ለ30 ቀናት እንደሚካሄድ ተናግረዋል።