የባህር ዳር ከተማ አካታች የኮሪደር ልማት የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባህር ዳር ከተማ አካታች የኮሪደር ልማት የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው
ባሕር ዳር፤ ጥር 1/ 2018(ኢዜአ)፡- የባህር ዳር ከተማ አካታች የኮሪደር ልማት የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑን የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ገለጸ።
የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ፍሬሰላም ዘገየ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተማዋ የተገነባው የኮሪደር ልማት የአካል ጉዳተኞችን የልማትና ማህበራዊ ተሳትፎ የሚያሳድግ ነው።
የኮሪደር ልማቱ የእግረኛ፣ የብስክሌትና የተሽከርካሪ መንገዶችን ለይቶ በመከናወኑ ቀደም ሲል ለአካል ጉዳተኞች እንቅስቃሴ አስቸጋሪ የነበረውን ሁኔታ እንደሚያቃልል ጠቁመዋል።
በተለይም ቀደም ባለው ጊዜ የእግረኛና የተሽከርካሪ መንገድ በተገቢው ባለመለየቱና፣ ያለቦታው የሚተከሉ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች እንዲሁም ያልተዘጉ ቦዮች ዓይነስውራንና በዊልቸር የሚንቀሳቀሱ አካል ጉዳተኞችን ለጉዳት ሲያጋልጡ እንደነበር አስታውስዋል።
በፌዴሬሽኑ የሴት አካል ጉዳተኞች ዘርፍ አስተባባሪ ወይዘሮ ባንቻምላክ አቤ በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማቱ የአካል ጉዳተኞችን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
ልማቱ ዐይነ ስውራንና ዊልቼር ተጠቃሚዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው ህይወታቸውን እንዲመሩ እድል የፈጠረ መሆኑንም አንስተዋል።
የከተማዋ የኮሪደር ልማት የአካል ጉዳተኞችን የልማት ተሳትፎን እንደሚያጠናክር ያነሱት ደግሞ የአማራ ክልል ዐይነ ስውራን ማህበር ሰብሳቢና የፌዴሬሽኑ የቦርድ አባል አቶ ክርስቲያን ይበልጣል ናቸው።
ከዚህ በፊት የሚገነቡት መሰረተ ልማት ስራዎች አካል ጉዳቶችን ታሳቢ ባለማድረጋቸው አካል ጉዳተኞች ከተሽከርካሪ ጋር በመጋፋት ለአደጋ ይጋለጡ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይህንን ችግር በማቃለል ከፍተኛ እገዛ ያደረገው የኮሪደር ልማትን በማጠናክር ወደ ሌሎች ከተሞች ማስፋት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የአማራ ክልል ከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ አማካሪ አቶ ሽቤ ክንዴ፤ እንደገለጹት በክልሉ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ ሰው ተኮርና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያማከለ ነው ብለዋል።
መሰረተ ልማት ዝርጋታዎቹ የስማርት ሲቲን ፕላን ደረጃን ጠብቀው በመከናወኑ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መሆኑን ገልጸዋል።
የከተማዋ መዋቅር ከተሞች ለስራ ፈጠራና ለማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ መሰረት የጣሉ ናቸው ብለዋል።
የከተሞቹ አካታች የመሰረተ ልማት ግንባታ በተለይም በዊልቼር፣ በክራንች እና በሌሎች የአካል ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ ወገኖች የልማት ተሳትፎን ለማሳደግ የማይተካ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።