ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በርካታ ፕሮጀክቶች ወደ ልማት እንዲገቡ ይደረጋል

አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2018 (ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ 50 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ልማት እንዲገቡ እንደሚደረግ የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አባስ መሐመድ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት ፕሮጀክቶቹ ከ2 ቢሊዮን 236 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል የተመዘገበባቸው ናቸው።

ኃላፊው እንደገለጹት በግብርና ፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ወደ ክልሉ ገብተው ለማልማት መሬት የጠየቁት ባለሃብቶች ተገቢውን መስፈርት አሟልተው በመገኘታቸው መሬቱ ተላልፎላቸው ወደ ተግባር እንዲገቡ ውሳኔ ተሰጥቷል።

ቀደም ሲል ከተዘጋጀው ለኢንዱስትሪ ዞኖች ግንባታ የሚሆን 4 ሺህ 97 ነጥብ 21 ሔክታር በተጨማሪ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ 216 ነጥብ 4 ሔክታር መሬት መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል።

እስከ አሁንም ለ35 ሺህ 235 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለም አስረድተዋል።

አክለውም በተለያየ ሥራ ዘርፍ ለተሰማሩ 19 አምራች ኢንዱስትሪዎች 305 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሥራ ማስኬጃ ብድር ማመቻቸት መቻሉንም ነው የገለጹት።

እንዲሁም አዳዲስ ለሚቋቋሙና ማስፋፊያ ለሚያካሂዱ ዘጠኝ አምራች ኢንዱስትሪዎች 89 ሚሊዮን ብር የመሳሪያ ሊዝ አቅርቦት ማመቻቸት መቻሉን ጠቅሰዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም