ቀጥታ፡

ሃዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥር 1/2018 (ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ዛሬም ቀጥሎ ሲውል ሶስት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። 

ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ሃዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የሁለት ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ሃዋሳ ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 13 ጨዋታዎች ስድስት ጊዜ ሲያሸንፍ በአራቱ ተሸንፏል። በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። በ13ቱ ጨዋታዎች 14 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 10 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ቡድኑ በ21 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።

የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ 13 ጨዋታዎችን አከናውኖ በአምስቱ ድል ሲቀናው አራት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በአምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 11 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ዘጠኝ ግቦችን አስተናግዷል። 

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ19 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ሃዋሳ ከተማ ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። ቅዱስ ጊዮርስ ከአምስት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

በሌላኛው መርሃ ግብር ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ድሬዳዋ ከተማ በ17 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ21 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ጨዋታው ሁለቱ ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።

መቀሌ 70 እንደርታ ከሸገር ከተማ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

መቀሌ 70 እንደርታ በ11 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ሸገር ከተማ በ13 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

በጨዋታው መቀሌ 70 እንደርታ ካሸነፈ ከወራጅ ቀጠና ይወጣል። ሸገር ከተማ ከአራት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም