ቀጥታ፡

ሪያል ማድሪድ አትሌቲኮ ማድሪድን በማሸነፍ በስፔን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ለፍጻሜ አለፈ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30/2018(ኢዜአ)፦  በስፔን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ሁለተኛ የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር ሪያል ማድሪድ አትሌቲኮ ማድሪድን 2 ለ 1 አሸንፏል።

ማምሻውን በሳዑዲ አረቢያ ኪንግ አብደላ ስፖርትስ ሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፌዴሪኮ ቫልቬርዴ በሁለተኛው እና ሮድሪጎ በ55ኛ ደቂቃ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

አሌክሳንደር ሶርሎዝ በ58ኛው ደቂቃ ለአትሌቲኮ ማድሪድ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

በጨዋታው አትሌቲኮ ማድሪድ በኳስ ቁጥጥር እና ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን በማድረግ የተሻለ የነበረ ቢሆንም ያገኛቸውን እድሎች በሚገባ መጠቀም አልቻለም።

የማድሪድ ደርቢ በሪያል ማድሪድ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሪያል ማድሪድ በስፔን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ፍጻሜ ከባርሴሎና የሚያደርገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

ባርሴሎና ትናንት አትሌቲኮ ቢልባኦን 5 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የሁለቱ ክለቦች የፍጻሜ ጨዋታ እሁድ ጥር 3 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም