በላሊበላ የገና በዓልን ከሃይማኖታዊ ስርአቱም ባለፈ የሰላም፣ የፍቅርና የመልካምነት መገለጫነቱን በሚያሳይ መልኩ አክብረናል- የበዓሉ ታዳሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
በላሊበላ የገና በዓልን ከሃይማኖታዊ ስርአቱም ባለፈ የሰላም፣ የፍቅርና የመልካምነት መገለጫነቱን በሚያሳይ መልኩ አክብረናል- የበዓሉ ታዳሚዎች
ወልዲያ፤ታህሳስ 30/2018(ኢዜአ )፡- በላሊበላ የገና በዓልን ከሃይማኖታዊ ስርአቱም ባለፈ የሰላም፣ የፍቅርና የመልካምነት መገለጫነቱን በሚያሳይ መልኩ አክብረናል ሲሉ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ታዳሚዎች ገለጹ።
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ገና በላሊበላ ከተማ በርካታ ምዕመናን፣ የውጭና የሀገር ውስጥ ታዳሚዎች በተገኙበት በላሊበላ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
ከተለያዩ አካባቢዎች በክብረ በዓሉ ላይ ከተገኙት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ታዳሚዎች የገና በዓል አከባበር ከሃይማኖታዊ ክብረ በዓልነቱ ባለፈ የሰላም፣ የፍቅርና የመልካምነት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት በዓሉ በላሊበላ ከተማ በደማቅ ስነ ስርአት መከበሩን ገልጸው የአካባቢው ማህበረሰብ አቀባበልና መስተንግዶ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ከታዳሚዎቹ መካከል ወይዘሮ ተውባ አለባቸው በቆይታቸው ሃይማኖታዊ ስርአቱን ከማከናወንም ባለፈ ከብዙዎች ጋር ማህበራዊ ትስስርና አብሮነትን ያጠናከርንበት ነው ብለዋል።
የላሊበላና አካባቢው ህብረተሰብ በጥሩ መስተንግዶ በመቀበል ፍቅርና አብሮነቱን በማሳየቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ እነዚህንና መሰል የካበቱ የማህበረሰብና የባህል እሴቶችን በመጠበቅ የሀገር ሃብት አድርጎ መዝለቅ የጋራ ሃላፊነታችን ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ሌላኛው የበዓሉ ታዳሚ አቶ በየነ አለማው፤ በቆይታቸው መንፈሳዊ ዓላማቸውን ከማሳካትም ባለፈ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመጡ እንግዶች ጋር ትውውቅ መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላትን በአብሮነትና በመደጋገፍ የማክበር የቆየ እሴት መኖሩን አንስተው የሁሉም ነገር መሰረት የሆነውን ሰላምን በማጽናት ትብብርና አብሮነትን ይበልጥ ማጠንከር ይገባል ብለዋል።
ከአዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ላሊበላ ተገኝተው የገና በዓልን ያከበሩት ወይዘሮ አበበች ወልደማርያም፤ ድንቅ በሆነው ስፍራ ከውጭና ከሀገር ውስጥ ታዳሚዎች ጋር በማክበራቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የሚያምርብንና ውበታችን አብሮነታቸን ነው ያሉት ወይዘሮ አበበች የሀገራችንን ሰላም በማረጋገጥ እምቅ የሆኑ ሃብቶችን በመጠበቅ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባናል ብለዋል።
በቆይታቸው የላሊበላ ከተማና አካባቢው ህዝብ ላደረገላቸው መልካም አቀባበል እና እንክብካቤ አመስግነዋል።