በጅማ ዞን እየተከናወኑ የሚገኙ የቱሪዝም ልማት ሥራዎች ለዘርፉ ዕድገት ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጅማ ዞን እየተከናወኑ የሚገኙ የቱሪዝም ልማት ሥራዎች ለዘርፉ ዕድገት ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ ነው
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 30/2018(ኢዜአ)፡- በጅማ ዞን እየተከናወኑ የሚገኙ የቱሪዝም መስህብ ልማት ሥራዎች ምቹ የመዳረሻ ምህዳር እየፈጠሩ መሆናቸውን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ።
ጅማ ዞን በሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ሀብት እምቅ አቅም ያለው ሲሆን በኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
ጅማ ከፍተኛ ጥራት ያለው የቡና ምርት ከሚገኝባቸው ቀጠናዎች አንዱ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቡና ማሳዎችንና የዝግጅት ሂደቶችን ለጎብኚዎች ክፍት በማድረግ የቡና ቱሪዝምን ለማሳደግ እየተሠራ ይገኛል።
በዞኑ የሚገኘው የደን ሽፋን ለአካባቢ ተስማሚ ቱሪዝም ወይንም ኢኮ-ቱሪዝም ትልቅ ዕድል ያለው ነው፡፡
የጅማ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ኒሜሪ አባተማም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እያንዳንዱ ወረዳ ቢያንስ አንድ የቱሪስት መዳረሻ እንዲኖረው ሰፋፊ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
እስካሁንም በ21 አዳዲስ ግንባታ ከተጀመረባቸው ወረዳዎች መካከል የሦስቱ ተጠናቀው ለተጠቃሚ ክፍት መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
እነኚህም ነዲ ጊቤ፣ ሊሙ ኮሳ እና ሊሙ ገነት ወረዳዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በሌሎቹም ቦታ የመለየት፣ በጀት የመያዝ እንዲሁም የማልማት ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
በዞኑ የሚገኙ እምቅ የቱሪዝም መስህቦችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጎብኚዎች በማስተዋወቅ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመርና የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም መሠረተ ልማት ወሳኝ በመሆኑም በጅማ ከተማ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እንዲገነቡ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በዞኑ በሚገኙ ቀበሌዎች የመንገድ መሠረተ ልማት የማሟላት ሥራ መከናወኑን ጠቁመው፤ የመዳረሻ ልማቱ ከኮሪደር ልማት ጋር በመሰናሰል እስከ አርሶ አደር ቀዬ እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
እነዚህ የልማት ሥራዎች የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ ዘርፉን በዘላቂነት ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
ይህም ዞኑን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል።