በኦሮሚያ ክልል የህግ የበላይነትን በማስከበር ሁለንተናዊ ልማትን የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የህግ የበላይነትን በማስከበር ሁለንተናዊ ልማትን የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የህግ የበላይነትን በማስከበር ሁለንተናዊ ልማትን የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ ገለጹ።
በክልሉ እስካሁን ከ22ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውን አስታውሰው ሰላምን በመግፋት በጥፋታቸው በቀጠሉት ላይ ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ፤ የክልሉን ወቅታዊ የሰላምና የልማት እንቅስቃሴ በማስመልከት ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የክልሉ መንግስት ከለውጡ ወዲህ ከገጠሙት ፈተናዎች መካከል በተወሰኑ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር እንደነበር አስታውሰው በዘላቂነት ለመፍታት ብዙ መሰራቱን አስረድተዋል።
በክልሉ የህግ የበላይነትን ከማስከበር በተጓዳኝ የተሳሳተ መንገድ ላይ የነበሩ አካላት ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ ጥረት ተደርጓል ብለዋል።
ከመንግስት የሰላም ጥሪ ባለፈ በአባ ገዳዎች፣ በሃዳ ሲንቄዎች፣ በሃይማኖት አባቶች እና በሀገር ሽማግሌዎች አማካኝነት ለሰላም ምላሽ እንዲሰጡ መሰራቱን አንስተዋል።
በዚህም መሰረት ከ22 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪን በመቀበል የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለሳቸውን ገልጸዋል።
ከቀድሞ ታጣቂዎቹ መካከል 10ሺህ የሚሆኑት የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ሲሆን ሌሎች እንደየፍላጎታቸው ወደ መደበኛ ህይወታቸው ተመልሰዋል ብለዋል።
የመስሪያ ቦታ እና 581 ሚሊዮን ብር ብድር ተመቻችቶላቸው ወደ ስራ የገቡ እንዳሉ ገልጸው ወደ ትምህርት እና ወደ መንግስት ስራም የተመለሱ እንዳሉ ጠቅሰዋል።
በክልሉ የህግ የበላይነትን በማስከበር ሁለንተናዊ ልማትን የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አረጋግጠዋል።
“በጽንፈኝነት ለጥፋት ዓላማ የተሰለፈ ሁሉ የትኛውንም ቋንቋ ቢናገር ጽንፈኛ ነው” ያሉት አቶ ሃይሉ የኦሮሞም ይሁን የአማራ ጽንፈኛ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ይጠናከራል ብለዋል።
በቅርቡ በሆሮ ጉዱሩ እና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች የተወሰኑ አካባቢዎች በጽንፈኞች ላይ ጠንካራ እርምጃ በመወሰዱ በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል።