ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገቷን ከካርቦን ልቀት ነጻ ለማድረግ ዓርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገቷን ከካርቦን ልቀት ነጻ ለማድረግ ዓርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነች ነው
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 30/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገቷን ከካርቦን ልቀት ነጻ ለማድረግ ለታዳጊ ሀገራት ትልቅ ትምህርት እየሰጠች መሆኗን ዓለም አቀፉ የታዳሽ ኃይል ኤጀንሲ ገለጸ።
አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) በዓለም አቀፉ የታዳሽ ኃይል ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ ሆነው የተሰየሙበትን የሹመት ደብዳቤ ለተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ፍራንቸስኮ ላ ካሜራ አቅርበዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የተላከን መልዕክት ማቅረባቸው ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ የኃይል ሽግግር ያላትን የማይናወጥ ቁርጠኝነትም ለዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።
ሀገራችን ከምትጠቀመው የኃይል ምንጭ ውስጥ ከ90 በመቶ የሚልቀው ከታዳሽ ኃይል የሚገኝ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል መሆኗን አስረድተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የንፋስ፣ የፀሐይ እና የጂኦተርማል ፕሮጀክቶች ለቀጣናው የኃይል ዋስትና እና ለአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም እያበረከቱት ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦም አስገንዝበዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ ተነሳሽነት እና ወደ ዝቅተኛ የካርቦን ኢኮኖሚ የምታደርገው ሽግግር ለመላው የአፍሪካ አኅጉር ዘላቂ ልማት እንደ ማሳያ የሚያገለግል መሆኑንም አመላክተዋል።
ዋና ዳይሬክተር ፍራንቸስኮ ላ ካሜራ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በዘላቂ ልማት ዘርፍ እያሳየች ያለውን ዓርአያነት ያለው አመራር አድንቀው፤ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገቷን ከካርቦን ልቀት ነጻ ለማድረግ ለታዳጊ ሀገራት ትልቅ ትምህርት እየሰጠች ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ 32ኛውን ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP32) እንድታስተናግድ መመረጧ ለዓለም አቀፉ የአየር ንብረት አጀንዳ ያላትን የላቀ ቁርጠኝነት እንደሚያሳይም በአድናቆት አንስተዋል።
ኤጀንሲው ኢትዮጵያ ቅድሚያ በምትሰጣቸው የኃይል ፕሮጀክቶች የቴክኒክ ድጋፍ ለመስጠት እና የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ለማሰባሰብ ቁርጠኛ መሆኑንም አረጋግጠዋል።