ቀጥታ፡

በወራቤ ከተማ ከዘጠኝ ሄክታር መሬት በላይ የሚሸፍን የወንዝ ዳርቻ የኮሪደር የልማት ሥራ እየተፋጠነ ነው

ወራቤ፤ ታኅሣስ 30/2018(ኢዜአ)፦ በወራቤ ከተማ ከዘጠኝ ሄክታር መሬት በላይ የሚሸፍን የወንዝ ዳርቻ የኮሪደር ልማት ሥራ እየተፋጠነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ያሲን ከሊል ገለጹ፡፡

ከንቲባው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከተማዋን ውብ፣ ፅዱ እንዲሁም ለኑሮ እና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት በልዩ ትኩረት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡


 

ከዚህም ውስጥ አንዱ የወንዝ ዳርቻ ልማት መሆኑን ጠቅሰው በከተማ አስተዳደሩና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ9 ሄክታር በላይ የሚሸፍን የወንዝ ዳርቻ ልማት ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የወንዝ ዳርቻ የኮሪደር ልማት ሥራው የከተማውን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ምቹ የመኖሪያ አካባቢ እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው የልማት ስራውን በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ከልማት ሥራው በተጨማሪ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ ካፍቴሪያ፣ የቅርጫትና የመረብ ኳስ መጫወቻ ሜዳ ፋውንቴን እንዲሁም ሰው ሰራሽ አነስተኛ ሐይቅ ማካተቱን ጠቅሰው የእነዚህ ግንባታዎች ስራም እየተጠናቀቀ  መሆኑን ጠቁመዋል።

ከ2 ሺህ 500 በላይ ሰዎችን መያዝ የሚችል ቲያትር አዳራሽ፣ የእግር ኳስ ሜዳና ሌሎች የግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡


 

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት አብዲ ዋሴ እና አቶ ሸርፈዲን ሹሜ፤ የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራው የወራቤ ከተማን ለነዋሪው ምቹ እንድትሆን ከማድረግ በተጨማሪ ከሌሎች አቻ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋት ተናግረዋል። 

በተለይም በከተማዋ የወንዝ ዳርቻን ለማልማት የተጀመረው ሥራ አካባቢው ቀድሞ የነበረውን መጥፎ ገጽታ በመቀየር  ለመዝናኛና ለሥራ ዕድል እንዲውል መደረጉን ገልጸዋል።


 

በከተማዋ እየታየ ያለው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እያደረግን ያለውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት ነዋሪዎቹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም