ቀጥታ፡

የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህንን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል

ደብረ ማርቆስ ፤ ታኅሣስ 30/2018(ኢዜአ)፦ በምስራቅ ጎጃም ዞን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህንን ተደራሽ በማድረግ  የማህበረሰቡን ጤና  ለመጠበቅ  የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የዞኑ ጤና መምሪያ ገለጸ።

የመምሪያው ሃላፊ አቶ የሽዋስ አንዷአለም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ የማህበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ ለቅድመ መከላከልና  ህክምና ጥራትን ማስጠበቅ ላይ በቅንጅት እየተሰራ ነው።

ለዚህም  በበጀት ዓመቱ ከ500 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መታቀዱን አንስተዋል።

እቅዱን ለማሳካት  በተደረገው ጥረት በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት ከ200 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።


 

የጤና መድህን አገልግሎቱ ዜጎች አንድ ጊዜ በከፈሉት አነስተኛ  ገንዘብ  የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን  ጤና   ለመጠበቅ ማገዙንም ጠቁመዋል።

የአገልግሎቱን ፍትሃዊነት ለማረጋገጥም  መክፈል ለማይችሉ ከ188ሺህ በላይ  ወገኖች መንግስት ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ በመደጎም ነጻ ህክምና እንዲያገኙ ማድረጉን አስረድተዋል። 

ቀደም ሲል በአገልግሎት አሰጣጡ የሚታይ የነበረን የመድሃኒት አቅርቦት ችግር ለመፍታትም በሁሉም ወረዳዎች የማህበረሰብ መድሃኒት ቤቶችን ለማስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዞኑ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች መካከል የጎዛምን ወረዳ የቡቅላ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ የውብ ምርት መለሰ ፤ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል በመሆናቸው  የቤተሰባቸውን ጤና  ለመጠበቅ እንደቻሉ  አስረድተዋል።

በአንድ ጊዜ አነስተኛ መዋጮ ዓመቱን ሙሉ ያለ ስጋት እንዲታከሙ በማድረጉና በአካባቢያቸው  የማህበረሰብ መድሃኒት ቤት መቋቋሙ በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኙ  ማስቻሉን ጠቁመዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት ከ442 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን በማቀፍ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም