ቀጥታ፡

በዞኑ የተራቆቱ አካባቢዎችን በአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ በማልማት ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

ነገሌ ቦረና፤ ታኅሣስ 30/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን የተራቆቱ አካባቢዎችን በአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ በማልማት ምርታማነትን ለማሳደግ  እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በጽህፈት ቤቱ የደን ጥበቃ የስራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ አልዬ አረባ እንዳሉት፤ በዞኑ የተራቆቱ አካባቢዎችን በአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ በማልማት ምርታማነትን ለማሳደግ  እየተሰራ ነው።

በአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራውም ከ52 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍኑ 105 ተፋሰሶች  እንደሚለሙ አስረድተዋል፡፡


 

የተፋሰስ ልማቱን ለማሳካትም 379 የቀበሌ አመራሮችና የልማት ጣቢያ ሰራተኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና መውሰዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዞኑ የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት ስራው ከ226 ሺህ በላይ  የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል፡፡

በበጋ ወራቱ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ እርከንን ጨምሮ ከእንስሳትና ሰው ንኪኪ ነጻ በማድረግ በመጪው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ ልማት ለመሸፈን መታቀዱን ተናግረዋል።

የተራቆተና የተጎዳ 38 ሺህ 244 ሄክታር የግጦሽ ሳር መሬት ከንክኪ የመከለል ስራም የተፋሰስ ልማቱ አካል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከበጋው ወራት የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ጎን ለጎን በክረምቱ የሚተከሉና ጥምር ጥቅም የሚሰጡ 36 ሚሊዮን ችግኞችን  የማፍላት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።


 

ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ልማት ስራዎች በዞኑ ድርቅን በመቋቋም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት  የራሳቸውን ድርሻ ማበርከታቸውን  አመልክተዋል፡፡

የልማት ስራውን ለመጀመር የሚያስችሉ የግብርና መሳሪያዎች በዞኑ ለሁሉም ወረዳዎች መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡

ዞኑ ቆላማና ዝናብ አጠር እንዲሁም በድርቅ የሚጠቃ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የእንስሳት እርባታ ስራ በስፋት እንደሚካሄድም ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም