ቀጥታ፡

በድሬዳዋ የተከናወኑ የተቀናጁ የተፋሰስ ልማቶች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አግዘዋል 

ድሬዳዋ፤ ታኅሣስ 30/2018(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተቀናጁ የተፋሰስ ልማቶች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ማገዛቸውን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ።

በአስተዳደሩ ባለፉት የለውጥ ዓመታት 56ሺህ ሄክታር የተራቆቱ መሬቶችን በተፋሰሶች በማልማት የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭን ስኬታማ ማድረጉም ተመልክቷል።

የፊታችን ጥር 3 ቀን 2018 ዓ.ም በድሬዳዋ 38 የገጠር ቀበሌዎች የሚጀመረውን የተፋሰስ ልማት አስመልክቶ ለአስተዳደሩ አመራሮችና ነዋሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ የተገኙት ከንቲባ ከድር ጁሃር፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በድሬዳዋ የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የጎርፍ አደጋዎችን ከማስቀረት ባለፈ የሌማት ትሩፋት ኢንሼቲቭን ስኬታማ አድርገዋል።

በተለይም በገጠሩ አካባቢ የተከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ተፋሰሶች የአፈር ለምነትን ለመመለስና የገጸ ምድርና ከርሰ ምድር የውሃ ሀብት እንዲጨምር ማድረጋቸውን አንስተዋል።

በተጨማሪም የጎርፍ ውሃን ለአነስተኛ መስኖ ልማቶች በማዋል ህብረተሰቡ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ እያስቻሉ ይገኛሉ ብለዋል።

ይህን ተሞክሮ በማስቀጠል በዘንድሮው የበጋ ወራት የተፋሰስ ልማት በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ህብረተሰቡ በመረባረብ እንዲያሳካም አስገንዝበዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኑረዲን አብደላ በሰጡት መግለጫ፤ በሚቀጥለው እሁድ በ 5 ሺህ 550 ሄክታር የተራቆቱ ተፋሰሶች ላይ የተለያዩ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራዎች እንደሚጀመር ተናግረዋል።


 

በ38ቱ የአስተዳደሩ የገጠር ቀበሌዎች ለአንድ ወር የሚከናወነው የተፋሰስ ልማት ከአፈርና ውሃ ጥበቃ ተግባራት በተጨማሪ ለመጪው ክረምት ለሚተከሉ የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኞች ጉድጓዶች ይዘጋጃሉ ብለዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት 56 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተካሄዱት የተፋሰስ ልማቶች የገጠሩን ህብረተሰብ የግብርናና የእንስሳት ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ከተረጂነት ወደ አምራችነት እያሸጋገሩ መሆኑን አንስተዋል።

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ስኬታማ በመሆኑ የማር፣ የወተት፣ የዶሮና የእንቁላል ምርቶችን ማሳደግ ማስቻሉን ጠቅሰው ይህም ህብረተሰቡ ተመጣጣኝ ምግብ እና ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ ማስቻሉን አስረድተዋል።


 

ዘንድሮ ከተፋሰሱ ልማት ጎን ለጎን የገጠሩን ህብረተሰብ በሙሉ የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት የማድረግ ስራ በትኩረት እንደሚሰራ የገለፁት ደግሞ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ኢብራሂም ዩሱፍ ናቸው።

አቶ ኢብራሂም አክለው እንዳሉት የገጠሩን ህብረተሰብ የኮሪደር ልማት ባለቤት የማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራም ይከናወናል።

ጥር 3 ቀን 2018ዓ.ም በሚጀመረው የተፋሰስ ልማት ስራ ላይ ከ37 ሺህ በላይ አርሶ እና አርብቶ አደሮች እንደሚሳተፉ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም