አሁናዊ ቁጥራዊ መረጃዎች ስለ 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ - ኢዜአ አማርኛ
አሁናዊ ቁጥራዊ መረጃዎች ስለ 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 30/2018(ኢዜአ)፦በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ሩብ ፍጻሜው ተሸጋግሯል።
በውድድሩ እስከ አሁን በተደረጉ 44 ጨዋታዎች 87 ግቦች ከመረብ ላይ አርፈዋል። ይህም በአማካይ በአንድ ጨዋታ 1 ነጥብ 98 ጎል ይቆጠራል ማለት ነው።
ናይጄሪያ 12 ግቦችን በውድድሩ ላይ በማስቆጠር ቀዳሚውን ስፍራ የያዘች ሀገር ናት። በተጨማሪም 64 የግብ ሙከራዎች (30 ኢላማቸውን የጠበቁ) ሙከራዎችን በማድረግ ከፍተኛውን ድርሻ ይዛለች።
በተጨማሪም ናይጄሪያ በየጨዋታው የ66 በመቶ የኳስ ድርሻ በመያዝ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘች ሀገር ሆናለች።
ቦትስዋና፣ ጋቦን እና ዩጋንዳ በተመሳሳይ ሰባት ጎሎችን በማስተናገድ በርካታ ግብ የተቆጠረባቸው ሀገር መሆናቸውን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።
የሞሮኮው ብራሂም ዲያዝ አራት ግቦችን በማስቆጠር የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው። የናይጄሪያው አዴሞላ ሉክማን አራት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል በርካታ የግብ እድሎችን ፈጥሯል።
እስከ አሁን በተደረጉ 44 ጨዋታዎች 173 ቢጫ ካርድ እና ሰባት ቀይ ካርዶች ተመዝግበዋል።
ከነዚህም ውስጥ ማሊ 11 ቢጫ እና ሁለት ቀይ ካርዶችን በመመልከት የቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች።
ማሊ እና ቱኒዚያ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በተመሳሳይ ሁለት የፍጹም ቅጣት ምቶችን በማግኘት በግንባር ቀደምትነት ይቀመጣሉ።
የአዘጋጇ ሞሮኮ ተጫዋቾች እስከ አሁን ባደረጓቸው ጨዋታዎች 77 ጊዜ ጥፋት በመፈጸም ጥሩ ያልሆነ ክብረ ወሰን ይዘዋል።
የሞሮኮ እና የደቡብ አፍሪካ ተጫዋቾች በተመሳሳይ 10 ጊዜ ከጨዋታ ውጪ በመሆን ብዙ ጊዜ ከጨዋታ ውጪ የሆኑ ተጫዋቾችን የያዙ ሀገራት ሆነዋል።
የ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ መርሃ ግብር ጥር 1 እና 2 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል። አጠቃላይ ውድድሩም እስከ ጥር 10 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች በአሃዛዊ መረጃዎች ላይ ለውጦች እንደሚኖሩ ይጠበቃል።