ቀጥታ፡

በድሬዳዋ በዘንድሮው የበጋ ወራት ከ3 ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ እየለማ ነው 

ድሬዳዋ፤ ታኅሣስ 30/2018(ኢዜአ)፦  በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮው የበጋ ወራት ከ3 ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም የአስተራረስ ስነ-ዘዴ በመስኖ እየለማ መሆኑን የአስተዳደሩ ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ገለፀ።

 የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ፣ባሳለፍነው ክረምት እና በበጋ ወራት በአነስተኛ መስኖ ልማቶች የተገኙ ውጤቶችን እና ቀጣይ ተግባራትን አስመልክተው ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።


 

ወይዘሮ ሚስራ እንዳሉት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በአስተዳደሩ የገጠር ቀበሌዎች የተከናወኑ የተቀናጁ የግብርና ልማት ስራዎች የተረጂነትና የጠባቂነት አስተሳሰብን በመናድ ተጨባጭ ውጤቶች እያመጡ ናቸው።

በተለይም የተከናወኑ የተፋሰስ፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር፣ የአነስተኛ መስኖና የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የህብረተሰቡ የምግብ ሉዓላዊነት እንዲረጋገጥ ማስቻላቸውን ተናግረዋል።

በአስተዳደሩ የገጠር ክላስተሮች የተከናወኑት የልማት ስራዎች በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ ማምረት ባህል እንዲሆን ማስቻላቸውን ጠቁመው፤ በዘንድሮው የበጋ ወራትም በ3 ሺህ 254 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም የሆርቲካልቸር ልማት እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።


 

በበጋው እየለሙ የሚገኙት የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የቡና ማሳዎች የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስገኙ ለአርሶ አደሩ፣ ለግብርና ባለሙያዎች እና አመራሮች የተሰጠው ስልጠና  ወሳኝና ቅንጅታዊ የአስራር ባህል እንዲዳብር ማድረጉን አንስተዋል።

ይህም ልማት በመጋቢት ወር መጨረሻ 839 ሺህ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ያስችላል ብለዋል።

በመጪው ጥር ወር የሚጀመረው የዘንድሮው የበጋ ተፋሰስ ልማትም የመስኖ ልማቱን ውጤታማነት ከማጠናከር ባሻገር አርብቶ አደሩ ከእንሰሳት ሃብቱ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።

የአዲጋ ፈለማ የገጠር ቀበሌ አርሶ አደር መሐመድ ኢብራሂም፤ የተጀመረው የተፋሰስ እና የመስኖ ልማት ስራ ማህበረሰቡን ከተረጂነት በማላቀቅ የምግብ ሉዓላዊነት እንዲያረጋግጥ እያገዙ መሆኑን ገልፀዋል።


 

ከቀናት በኋላ የሚጀመረውን የተፋሰስ ልማት ስኬታማ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝግጅቶች ተጠናቀው ወደ ስራ ለመግባት እየተጠባበቁ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከድሬዳዋ አስተዳደር ህዝብ አንድ ሶስተኛውን እና የአስተዳደሩን መልክዓ ምድር 96 በመቶ የሚሸፍነው የገጠሩን ህብረተሰብ የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በመተግበር ላይ የሚገኙት የልማት ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም