ለኢንተርፕራይዞች የሚሰጠው የክህሎት ማበልጸጊያ ስልጠና ውጤታማነትን እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለኢንተርፕራይዞች የሚሰጠው የክህሎት ማበልጸጊያ ስልጠና ውጤታማነትን እያሳደገ ነው
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 30/2018(ኢዜአ)፦ በኢንተርፕራይዝ ለተሰማሩ ዜጎች የሚሰጠው የክህሎት ማበልጸጊያ ስልጠና ውጤታማነትን እያሳደገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ገለጹ።
የአዲስ አበባ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ከመደበኛ መማር ማስተማር ተልዕኳቸው ጎን ለጎን የወጣቶችን የሥራ ውጤታማነት የሚያዳብር የክህሎት ማበልጸጊያ ሥልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አመራሮችም፤ የመዲናዋን ኢንተርፕራይዞች ውጤታማነት የሚያሳድግ ተከታታይ የክህሎት ድጋፍ ስልጠና እየሰጡ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ዋና ዲን መስፍን ቸሩ፤ የኢንተርፕራይዞችን ምርታማነት የሚያጎለብት በክህሎት የበለጸገ የሰው ሃይል የማፍራት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በተለይም በአውቶሞቲቭ፣ ሆቴልና ቱሪዝም፣ ጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ የኢንተርፕራይዞችን የምርትና አገልግሎት ጥራት የሚያስጠብቅ የክህሎት ስልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል።
የኮልፌ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ዋና ዲን ቢንያም አወቀ (ዶ/ር)፤ በአሁኑ ወቅት የ1ሺህ 100 ኢንተርፕራይዞችን ውጤታማነት የሚያሻሽል የክህሎት ማበልጸጊያ ስልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል።
የኢንተርፕራይዝ ድጋፍና ክትትልም የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማፋጠን የተመዘገቡ ውጤቶችን በጥናትና ምርምር በመለየት ውስንነቶች እንዲቀረፉላቸው የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን ሸላማ ንጉሱ፤ ለኢንተርፕራይዞች የሚሰጠው የክህሎት ማበልጸጊያ ስልጠና የአምራች ኢንዱስትሪ ሽግግሩን በማሳለጥ በተኪ ምርት ውጤት እየተገኘ ነው ብለዋል።
በማኑፋክቸሪንግ፣ ከተማ ግብርናና መሠል መስኮች ለተሰማሩ ኢንተርፕራዞች ውጤታማ ማኅበራትን ማፍራት ያስቻለ ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የሥራና ክህሎት ቢሮ የኢንተርፕራይዝና ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ኃላፊ ሚደቅሳ ከበደ፤ የኮሌጆች የክህሎት ማበልፀጊያ ስልጠና ለኢንተርፕራይዞች ውጤታማነት መሰረት ነው ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችም የሥራ ፈላጊ ዜጎችን የክህሎት ዝንባሌ ታሳቢ በማድረግ የሚሰጡት ትምህርትና ስልጠና ኢንተርፕራይዞችን ውጤታማ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።