ቀጥታ፡

በመስኖ ልማት በመታገዝ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጉዞ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 30/2018(ኢዜአ)፦ በመስኖ ልማት በመታገዝ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው ጉዞ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውኃ፣ መስኖና ቆላማ አካባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አወቀ አምዛዬ (ዶ/ር) ገለጹ።

መንግሥት ለመስኖ ልማት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በግብርናው መስክ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል።

በዚህም የአርሶ አደሩን ህይወት ከመቀየር አልፎ እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አስቻይ መሆኑ ተመላክቷል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውኃ፣ መስኖና ቆላማ አካባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አወቀ አምዛዬ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ ያላትን የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር የውኃ ሀብት በመጠቀም በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፊ የእርሻ መሬት ያላት ሀገር ናት፡፡


 

የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ይህንን የመሬትና የውኃ ሀብት በመስኖ ማልማት ወሳኝ በመሆኑ በመንግሥትና በሕብረተሰቡ ቅንጅት ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች በአነስተኛ መስኖ ላይ የግብርና ልማት እያለሙ የሚገኙ አርሶ አደሮች የአትክልት፣ ፍራፍሬና የሰብል ምርቶችን በማምረት ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በዓመት ሦስት ጊዜ ለማምረትና በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰተውን የዝናብ መቆራረጥ ተጽዕኖ መቋቋም የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም እንደ ሀገር የተያዘውን የምግብ ሉዓላዊነት እውን ለማድረግ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

መንግሥት ከዚህ ቀደም የተጀመሩ የመስኖ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ከማድረጉ በላይ አሁን ላይ የተጀመሩ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆኑ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በዘርፉ የተያዘው ዕቅድ እውን እንዲሆንና የኅብረተሰቡ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የክትትልና ቁጥጥር ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የመስኖ ፕሮጀክቶች ፕሮግራም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አሸናፊ ሊካሣ በበኩላቸው፤ በአብዛኛው የሀገራችን ኢኮኖሚ የተመሰረተው በግብርና ላይ መሆኑን አንስተው መስኖን በመጠቀም ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

የመስኖ ልማት ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ ግብዓቶችን ለማምረት፣ ዘመናዊ የአመራረት ዘዴን ለማላመድና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በፌዴራል መንግሥት የተሰሩ የመስኖ መሰረተ ልማቶችን፣ ግድቦችን፣ የመስኖ ቦዮች እና ወንዝ መቀልበሻዎችን የማስተሳሰር ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

አነስተኛ መስኖዎች በክልል ደረጃ እንደሚሰሩ አንስተው፤ ለስኬታማነቱ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ተገንብተው አገልግሎት ላይ የሚገኙ የመስኖ ፕሮጀክቶች በሚሰጡት ዘርፈ ብዙ ጥቅም የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ እየቀየሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም