ቀጥታ፡

ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከምክክር የተሻለ አማራጭ ባለመኖሩ እድሉን በአግባቡ መጠቀም ይገባል

ሀዋሳ፤ ታኅሣስ 30/2018(ኢዜአ)፦ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከምክክር የተሻለ አማራጭ ባለመኖሩ እድሉን በአግባቡ መጠቀም ይገባል ሲሉ የሲዳማ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አካታችና አሳታፊ የምክክር ሂደት በማካሄድ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሲዳማ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ከምክክር የተሻለ የመፍትሄ አማራጭ አለመኖሩን አንስተዋል።

በሲዳማ ባህል ''አፊኒ''ን ጨምሮ ግጭትና አለመግባባቶች የሚፈቱበት ባህላዊ ስርዓት የተለመደ መሆኑን ያነሱት የሃገር ሽማግሌዎቹ እንደ ሀገር ደግሞ ተመካክሮ ችግሮችን መፍታት የሚወደድና የሚደገፍ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ ክልሎች ያሉ መሰል እሴቶች ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት አጋዥ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡


 

ከሀገር ሽማግሌዎቹ መካከል አቶ ሻምበል በላይ፤ በምክክር ችግሮች እንዲፈቱ መስራት በተለይም የሀገር ሽማግሌዎች ሚና መሆኑን ገልጸው ለሀገራዊ የምክክር ሂደቱ መሳካት ሚናችንን መወጣታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።

ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ በምክክር ምዕራፉና አጠቃላይ ሂደቱን በማገዝና በመደገፍ የሲዳማ የሀገር ሽማግሌዎች እስካሁን የበኩላቸውን ማድረጋቸውን አንስተው ይህንንም እስከ መጨረሻው የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በጋራ ከመመካከር በላይ የተሻለ የችግር መፍቻ ቁልፍና ዘላቂ የመፍትሄ አማራጭ እንደሌለ አንስተው፣ ይህን ዕድል በአግባቡ መጠቀም ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ሌላኛው የሀገር ሽማግሌ አቶ ካሌ አራፎ፤ ጠንካራ ሀገራዊ አንድነትንና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር ምክክር ወሳኝ መሆኑን አንስተው በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።


 

የምክክሩ ውጤት የግጭትና አለመግባባት ምክንያቶችን በመቋጨት አንድነትን ማጠናከርና ሰላምን ማስፈን በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን እድሉን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሁሉም የጋራ ቤት ናት ያሉት የሀገር ሽማግሌው አቶ ቦና ቦቆንቻ ፤ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት በየአካባቢያቸው በንቃት እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡


 

ለሀገር ሰላም፣ ለህዝቦች አንድነትና አብሮነት የምክክሩ ሚና የላቀ መሆኑን አንስተው ለስኬቱ በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም