ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሳተላይቶች ያመነጯቸው መረጃዎች ጉልህ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አበርክተዋል 

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 30/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሳተላይቶች ያመነጯቸው መረጃዎች ጉልህ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማበርከታቸውን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ገለጸ።

በሚቀጥለው ዓመትም ሶስተኛዋን የመሬት ምልከታ የመረጃ ሳተላይት ወደ ሕዋ ለማምጠቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን ሳተላይት ኢቲ-አር.ኤስ.ኤስ1 (ET-RSS1) እንዲሁም ሁለተኛው ኢቲ-ስማርት-አር.ኤስ.ኤስ (ET-SMART-RSS)  የተሰኙ ሁለት የመረጃ ሳተላይቶችን ወደ ሕዋ ማምጠቋ ይታወሳል።


 

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ቀደም ሲል ወደሕዋ የተላኩ ሁለት የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች የአገልግሎት ጊዜያቸውን አጠናቀዋል።

የመሬት ምልከታ የመረጃ ሳተላይቶቹም በርካታ ቴክኖሎጂያዊና ሳይንሳዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የምግብ ዋስትና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በተፈጥሮ ሃብት አያያዝ የግብርና መስኮች፣ በከተማ ፕላንና መሠረተ ልማት፣ በሀገር ሉዓላዊነትና ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ ጠቀሜታ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም በሚቀጥለው ታኅሳስ 2019 ዓ.ም በምስል ጥራትና የጊዜ ቆይታ አቅም ያላት ኢቲ-አር.ኤስ.ኤስ 2 (ET-RSS2) የተሰኘች ሳተላይት ወደ ሕዋ ለማምጠቅ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

በቀጣይ የምትመጥቀው ኢቲ-አር.ኤስ.ኤስ 2 ሳተላይት ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመታጠቅ በሕዋ ላይ የአምስት ዓመታት የጊዜ ቆይታ እንዲኖራት ታሳቢ መደረጉ ነው የተገለጸው።

ከዚህ ቀደም ወደ ሕዋ ከተላኩ ሳተላይቶች የተገኘውን መረጃ የመቀበል፣ የመተንተን፣ የመቆጣጠርና የጥገና አቅም መፈጠሩን አስረድተዋል።

ሦስተኛዋን ሳተላይት ለማምጠቅ እየተደረገ የሚገኘው ጥረትም የኢትዮጵያን የሳተላይት ልማት አቅም በተግባር የሚያሳይ እንደሚሆን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም