ቀጥታ፡

ለሀገራዊ ምክክሩ ግብ ስኬት የሚጠበቅብንን አስተዋጽኦ እናጠናክራለን - የሲቪክ ማህበራት

ባህር ዳር ፤ ታኅሣስ 30/2018(ኢዜአ)፦ ለሀገራዊ ምክክሩ ግብ ስኬት የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በአማራ ክልል የሚገኙ የሲቪክ ማህበራት ገለጹ።

የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ፍሬሰላም ዘገዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አለመግባባት እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ የተራራቁ ሃሳቦች የፈጠሩትን ችግሮች በውይይት ፈትቶ በህዝቦች መካከል አንድነትና መግባባትን ለማጠናከር የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ትልቅ ዕድል ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይህን ለማሳካት በጀመረው ጥረት በንቃት በመሳተፍ ለምክክር የሚሆን አጀንዳዎችን ማቅረባቸውን ጠቁመዋል።


 

የአጀንዳ ልየታና ማሰባሰብ መድረክ ላይ አካል ጉዳተኞችን በንቃት በማሳተፍ አሉ ያሏቸውን ችግሮች በአጀንዳ ለማስያዝ ተችሏል ብለዋል።

‎ችግሮችን በውይይት በመፍታት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት በሚደረገው ጥረትም የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን አስረድተዋል።

‎‎የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወጣት ጋሻው አዘነ በበኩሉ እንዳለው፤ በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የሚስተዋሉ ልዩነቶችና አለመግባባቶችን ተመካክሮ ‎መፍታት ለጠንካራ ሀገር ምስረታ አስፈላጊ ነው።


 

‎‎በኮሚሸኑ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ከክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣቶችን በማሳተፍ አሉ የሚሏቸውን ዋና ዋና ችግሮች ለይተው በአጀንዳ ማስገባታቸውን ገልጿል።

‎‎ኮሚሽኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ ምክክር በማድረግ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠርና የተሻለ ሀገር ለመገንባት እያደረገ ያለው ጥረት የሚደገፍ መሆኑንም ተናግሯል።

‎ሀገራዊ ምክክር የተሻለች ሀገር ለመገንባት ትልቅ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ወጣቶች የምክክር ተግባሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከኮሚሽኑ ጎን በመሰለፍ እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም