የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ14ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራል።
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ሲዳማ ቡና ከአርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታውን ያደርጋል።
ሲዳማ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው 13 ጨዋታዎች መካከል ስምንቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በአራት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በ13ቱ ጨዋታዎች ላይ 18 ጎሎችን ሲያስቆጥር ስድስት ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ቡድኑ በ28 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።
ተጋጣሚው አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ምንም ጨዋታ ያለሸነፈ ብቸኛ ቡድን ነው። ስድስት ጊዜ ሲሸነፍ በሰባቱ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ላይ አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር 14 ጎሎችን አስተናግዷል።
አርባምንጭ ከተማ በሰባት ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዟል።
ሲዳማ ቡና ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል። አርባምንጭ ከተማ በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
በሌላኛው መርሃ ግብር ምድረገነት ሽሬ ከነጌሌ አርሲ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ምድረገነት ሽሬ እስከ አሁን በሊጉ 13 ጨዋታዎችን አድርጎ አራት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ በአራቱ ተሸንፏል። አምስት ጊዜ ነጥብ ጥሏል። 11 ግቦችን ሲያስቆጥር ዘጠኝ ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ17 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።
አዲስ አዳጊው ነጌሌ አርሲ በሊጉ ባከናወናቸው 13 ጨዋታዎች በስድስቱ ሲያሸንፍ በሶስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። አራት ጊዜ አቻ ወጥቷል። 15 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ዘጠኝ ግቦች ተቆጥረውበታል።
ነጌሌ አርሲ በ22 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
ምድረገነት ሽሬ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ፣ ነጌሌ አርሲ በድል ጉዞው ለመቀጠል ይጫወታሉ።
ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከአዳማ ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ10 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። አዳማ ከተማ በ21 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።