ቀጥታ፡

የማድሪድ ደርቢ በስፔን አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ 

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 30/2018(ኢዜአ)፦ በስፔን የአሸናፊዎች ዋንጫ አትሌቲኮ ማድሪድ እና ሪያል ማድሪድ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው። 

ጨዋታው ምሽት አራት ሰዓት ላይ በኪንግ አብደላ ስፖርትስ ስታዲየም ይካሄዳል።

ሁለቱ ክለቦች በስፔን የአሸናፊዎች ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለአምስተኛ ጊዜ ነው። 

ከዚህ ቀደም በተደረጉት አራት ጨዋታዎች ሪያል ማድሪድ ሁለት ጊዜ ሲያሸነፍ አትሌቲኮ ማድሪድ በአንዱ ድል ሲቀናው በአንዱ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል። 

ሁለቱ ቡድኖች ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ በ2024 በግማሽ ፍጻሜ ሲሆን በወቅቱ ሪያል ማድሪድ 5 ለ 3 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፏል። 

በወቅቱ ሪያል ማድሪድ በፍጻሜው ባርሴሎናን 4 ለ 1 በማሸነፍ ዋንጫ አንስቷል። 

ከአራቱ ጨዋታዎች አንዱ (እ.አ.አ በ2014) ፍጻሜው በደርሶ መልስ ሲካሄድ የተደረገ ነው። 

ሪያል ማድሪድ የስፔን አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን 13 ጊዜ ሲያነሳ አትሌቲኮ ማድሪድ ሁለት ጊዜ ውድድሩን አሸንፏል።

የሁለቱ ቡድኖች አሸናፊ በፍጻሜው ከባርሴሎና ጋር ይጫወታል።

ባርሴሎና ትናንት አትሌቲኮ ቢልባኦን 5 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የፍጻሜው ጨዋታ እሁድ ጥር 3 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

የስፔን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በስፔን ላሊጋ እና በስፔን ጥሎ ማለፍ ዋንጫ በተመሳሳይ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን የያዙ ክለቦች የሚሳተፉበት ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም