ቀጥታ፡

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አርሰናል እና ሊቨርፑል የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30/2018(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት መርሃ ግብር አርሰናል እና ሊቨርፑል ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 5 ሰዓት ላይ በኤምሬትስ ስታዲየም ይካሄዳል።

አርሰናል በዘንድሮው የውድድር ዓመት ባደረጋቸው 20 ጨዋታዎች 15 ጊዜ ሲያሸንፍ በሁለቱ ተሸንፎ በሶስት አቻ ተለያይቷል።

መድፈኞቹ በጨዋታዎቹ 40 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ 14 ግቦች ተቆጥረውባቸው በ48 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዘዋል።

ተጋጣሚው ሊቨርፑል በሊጉ ባደረጋቸው 20 ጨዋታዎች 10 ጊዜ ሲያሸንፍ ስድስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዶ በአራቱነጥብ ጥሏል።

በጨዋታዎቹ 32 ግቦች ሲያስቆጥሩ 28 ግቦች ተቆጥረውበታል። 

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል በ34 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
  
አርሰናል እና ሊቨርፑል በሁሉም ውድድሮች እስከ አሁን 245 ጊዜ ተገናኝተዋል። 

ሊቨርፑል 96 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዝ አርሰናል በበኩሉ 83 ጊዜ ሲያሸንፍ 66 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። 

በፕሪሚየር ሊጉ 67 ጊዜ ተገናኝተው ሊቨርፑል 26 ጊዜ ሲያሸንፍ አርሰናል በ18ቱ ድል ቀንቶታል። በቀሪ 23 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። 

ባለፉት አምስት የሊግ የእርስ በርስ ጨዋታቸው ሁለቱም በተመሳሳይ አንድ ጊዜ ሲያሸንፉ በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በዘንድሮ የሊግ መርሃግብር በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ሊቨርፑል 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል። 

አርሰናል ካሸነፈ ከተከታዩ ማንችስተር ሲቲ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ስምንት ከፍ ያደርጋል። 

የ47 ዓመቱ አንቶኒ ቴይለር የሁለቱን ቡድኖች ተጠባቂ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም