ቀጥታ፡

ማንችስተር ሲቲ ነጥብ ጣለ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 29/2018(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ121ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ማንችስተር ሲቲ እና ብራይተን አንድ አቻ ተለያይተዋል።

ማምሻውን በኢትሃድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አርሊንግ ሃላንድ በ41ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠራት ጎል ማንችስተር ሲቲን መሪ አድርጓል።

ሃላንድ በሊጉ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ወደ 20 በማሳደግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን አጠናክሯል።

ካሩ ሚቶማ በ60ኛው ደቂቃ ለብራይተን የአቻነቷን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ማንችስተር ሲቲ ከእረፍት መልስ ጨዋታውን ማሸነፍ የሚችልባቸውን እድሎች መጠቀም አልቻለም። የቡድኑ የተከላካይ ክፍል በጉዳት መሳሳት ለአደጋ ተጋላጭ አድርጓታል።

በሊጉ ለሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች አቻ የወጣው ማንችስተር ሲቲ በ43 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

ከአርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት የማጥበብ እድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ብራይተን በ29 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል።


 

በሌሎች የሊጉ መርሃግብሮች በርንሌይ እና ማንችስተር ዩናይትድ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።

በተርፍ ሙር ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቤንጃሚን ሼስኮ ሁለቱንም ግቦች ለዩናይትድ ከመረብ ላይ አሳርፏል።

የዩናይትዱ ተከላካይ አይደን ሄቨን በራሱ ላይ እና ጄይደን አንቶኒ ለበርንሌይ ጎሎቹን አስቆጥረዋል። 

ማንችስተር ዩናይትድ ከሩበን አሞሪም ስንብት በኋላ በጊዜያዊ አሰልጣኝ ዳረን ፍሌቸር እየተመራ የመጀመሪያ ነጥቡን ሲያገኝ በ32 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል።


 

ፉልሃም ቼልሲን 2 ለ 1 ሲያሸንፍ ራውል ሂሜኔዝ እና ሃሪ ዊልሰን የማሸነፊያ ግቦቹን ሲያስቆጥሩ ሊያም ዴላፕ ብቸኛውን ጎል ለቼልሲ ከመረብ አሳርፏል።

የቼልሲው ማርኮ ኩኮሬያ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

በስልኸረስት ፓርክ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ክሪስታል ፓላስ እና አስቶንቪላ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

አስቶንቪላ በ43 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

ብሬንትፎርድ ሰንደርላንድን 3 ለ 0 ሲረታ ቦርንማውዝ ቶተንሃም ሆትስፐርስን 3 ለ 2 እና ኒውካስትል ዩናይትድ ሊድስ ዩናይትድን 4 ለ 3 አሸንፈዋል።

ኤቨርተን ከዎልቭስ ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም