ቀጥታ፡

ኪነ-ጥበብ ትውልድን በስነ-ምግባር ለመቅረጽና የሀገርን የልማት ጉዞ ለማሳካት ወሳኝ መሳሪያ ነው

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 29/2018 (ኢዜአ)፦ ኪነ-ጥበብ ትውልድን በስነ-ምግባር ለመቅረጽና የሀገርን የልማት ጉዞ ለማሳካት ወሳኝ መሳሪያ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ኪነ ጥበብ ቢሮ ኃላፊ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) ገለጹ።

የአዲስ ታለንት ሾው የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር በሙዚቃ፣በሰርከስና በትወና ዘርፍ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።


 

በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ኪነ ጥበብ ቢሮ ኃላፊ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር)፥ ኪነ-ጥበብ አዎንታዊ አስተሳሰብን በማስረጽ ረገድ ከፍተኛ አቅም አለው ብለዋል።

ኪነ-ጥበብ መዝናኛ ብቻ ሳይሆን የሰላም፣የአንድነትና የልማት መሣሪያ ነው ያሉት ኃላፊዋ፥ ትውልድን በመልካም ስነ-ምግባር በማነጽ ረገድም የማይተካ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

መንግስት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ጠቅሰው፥በመዲናዋ ኪነ ጥበቡን የሚደግፉ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።


 

አዲስ ታለንት ሾው ወጣቶች ተሰጥኦዋቸውን እንዲያወጡ በማድረግ ተተኪ የጥበብ ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ ጉልህ ሚና እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቀጣይም ከተማ አስተዳደሩ ለኪነ ጥበብ ዘርፉ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።


 

የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ካሳሁን ጎንፋ በበኩላቸው፤ ሚዲያው ለኪነ-ጥበብ ዘርፍ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን በማንሳት አዲስ ታለንት ሾው የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም