የገና በዓል ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም፣ ፍቅር እና ትህትና የተገለጠበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የገና በዓል ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም፣ ፍቅር እና ትህትና የተገለጠበት ነው
ላሊበላ፤ታኅሣስ 29/2018 (ኢዜአ)፦ የገና በዓል ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም፣ ፍቅር እና ትህትና የተገለጠበት ነው ሲሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤሊያስ አብርሃ ተናገሩ።
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) በርካታ ምዕመናን፣ የውጭና የሀገር ውስጥ ታዳሚዎች በተገኙበት በላሊበላ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
በዓሉም አንድነት ፍቅርና አብሮነትን ማጠናከርና ሰላምን በማጽናት ለሀገር ሰላም በጋራ መትጋት አስፈላጊ መሆኑን አጽኖት በመስጠት መልእክቶች ተላልፈውበታል።
በበዓሉ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤሊያስ አብርሃ፤ የክርስቶስ የልደት በዓል ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም፣ ፍቅር እና ትህትና የተገለጠበት ነው ብለዋል።
በመሆኑም ልደቱን በፍቅርና ደስታ ስናከብር ስለ ሀገር ሰላምና አብሮነት ይበልጥ ተቀራርበን በመስራት መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ፤ በቅዱስ ላሊበላ የሚዘመረው የቤዛ ኩሉ ዓለም ሥርዓት የሰው እና የመላእክት ዝማሬ ምሳሌ ስለመሆኑ አንስተዋል።
የገና በዓል በኢትዮጵያ በፍቅር፣ በሰላም፣ በደስታ እና አብሮነት እየተከበረ እስካሁን መዝለቁን ገልጸው እሴቱና ትውፊቱ ተጠብቆ መዝለቅ አለበት ብለዋል።
በዓሉን ስናከብር ስለ ሀገር ሰላም፣ አንድነት እና ለፍቅር በጋራ በመቆም መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
የገና በዓል በላሊበላ ከተማ የሰሜንና ደቡብ ወሎ እንዲሁም የከሚሴ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ኤርምያስን ጨምሮ ሌሎችም ሊቃነ ጳጳሳት፣ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶችና እንግዶች በታደሙበት በደማቅ ስነ ስርአት ተከብሯል።