ቀጥታ፡

በበዓላት ወቅት ለአቅመ ደካማ ወገኖች የሚደረጉ ማዕድ የማጋራት የበጎነት ተግባራትን ማጠናከር ይገባል

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 29/2018 (ኢዜአ)፦በበዓላት ወቅት ለአቅመ ደካማና ለተቸገሩ ወገኖች ያለን የማካፈልና የአብሮነት በጎ ሥራዎች ዘወትር ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለጸ።

‎ኮሚሽኑ የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ከ500 በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካማና የተቸገሩ ወገኖች በገላን ጉራ የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከል ማዕድ የማጋራት መርሀ ግብር አካሂዷል።

‎‎የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ይመር ከበደ በወቅቱ እንደገለጹት በበዓላት ወቅት የሚደረጉ የማዕድ ማጋራትና ሌሎች በጎ ተግባራት የመረዳዳት፣ የመተሳሰብ እና የአብሮነት እሴትን የሚያጎለብቱ ናቸው።

የገና በዓል የፍቅርና የአብሮነት መገለጫ በመሆኑ አቅም የሌላቸውን ወገኖች በማሰብ እና ካለን ላይ በማካፈል አብሮ ማክበር ይገባል ብለዋል።

‎የከተማዋ ነዋሪዎች እና ባለሀብቶች በየአካባቢያቸው ማዕድ በማጋራትና በሌሎች በጎ ተግባራት በዓሉን ከአቅመ ደካማና ከተቸገሩ ወገኖች ጋር በደስታ እያሳለፉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በበዓላት ወቅት የሚደረጉ የበጎነት ተግባራትን ዘወትር ባህል አድርጎ ማስቀጠል እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

‎የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን መሰል የበጎ አድራጎት ስራዎችን ባለሀብቶችንና ነዋሪዎችን በማስተባበር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።


 

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ሚጀና በበኩላቸው፥ ክፍለ ከተማው ከልማት ስራዎች ጎን ለጎን አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሰው ተኮር ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል።

በማዕድ ማጋራቱ ላይ የተገኙ አቅመ ደካማ ወገኖች ከተማ አስተዳደሩ በዓሉን በደስታ እንዲያከብሩ በማድረጉ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም