ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቱሉ አራራ የተቀናጀ ሞዴል መንደርን በይፋ መረቁ 

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 29/2018 (ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)የቱሉ አራራ የተቀናጀ ሞዴል መንደርን ዛሬ በይፋ መርቀዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤  ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ጋር በመሆን፣ የክረምት በጎ አድራጎት መርሃ ግብርን ወደ ላቀ ከፍታ ያሸጋገረውን የቱሉ አራራ የተቀናጀ ሞዴል መንደርን በይፋ መመረቃቸውን ገልጸዋል። 


 

ሞዴል መንደሩ በሰባት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ቤት ሁለት መኝታ ክፍሎችን ጨምሮ በአጠቃላይ አምስት ክፍሎች እንዲኖሩት ተደርጎ ደረጃውን ጠብቆ የተገነባ መሆኑን ጠቁመዋል። 


 

መንደሩ በቤተሰብ ደረጃ ለ150 ዜጎች ምቹና ጽዱ መኖሪያ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን  የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሠረተ ልማት አቅርቦቱም የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የኤሌክትሪክና የሶላር ኃይል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ስፍራ እና የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን እንደሆኑም አመልክተዋል። 


 

የነዋሪዎቹን የኑሮ ደረጃ በዘላቂነት ለማሻሻል መንደሩ የምርትና የገበያ ሰንሰለትን ያካተተ የተቀናጀ አሰራርን ዘርግቷል ሲሉም ተናግረዋል።


 

ይህ የልማት ስራ የወተት ላሞች እና የዶሮ እርባታን እንዲሁም የጓሮ አትክልት ልማትን አጣምሮ የያዘ ሲሆን፣ እስከ መገበያያ ስፍራ የሚደርስ የተቀናጀ የንግድ ሰንሰለት መፍጠሩን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ላይ የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም