ቀጥታ፡

በዓልን ከተቸገሩ ወገኖች ጋር አብሮ ማሳለፍና ያለን ማካፈል የኢትዮጵያዊነት መገለጫ  ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ታኅሣስ 29/2018 (ኢዜአ)፦ የበዓል ወቅትን ከተቸገሩ ወገኖች ጋር አብሮ ማሳለፍና ያለን ማካፈል የኢትዮጵያዊነት መገለጫ እሴት መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የገና በዓልን በጉለሌ ተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ተገኝተው ማዕድ በማጋራት በዓሉን ከአቅመ ደካማና ከተቸገሩ ወገኖች ጋር አክብረዋል። 


 

ከንቲባ አዳነች ባስተላለፉት መልዕክት፤ በበዓል ወቅት ያለን ማካፈል፣ የተቸገሩትን ማሰብና አብሮነትን ማጠናከር የኢትዮጵያዊነት መገለጫ እሴት ነው ብለዋል።

በዛሬው ዕለት ይህን መልካም እሴት በተግባር ለመግለጽ በከተማዋ በሚገኙ 26 የምገባ ማዕከላት ማዕድ በማጋራት በዓሉ በጋራ እየተከበረ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከንቲባዋ በጉለሌ ተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በመገኘት ከአባቶች፣ ከእናቶችና ከሕፃናት ጋር የገና በዓልን አክብረናል ብለዋል።


 

ማዕድ ከማጋራት ባሻገር ሁልጊዜም የነዋሪዎችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የተሻለች አዲስ አበባን በጋራ ለመገንባት አስተዳደሩ  በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመዲናዋ አቅመ ደካማ ወገኖችን፣ የሀገር ባለውለታዎችንና የተቸገሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ በሚደረገው በጎ ተግባር ላይ ለሚሳተፉ ባለሀብቶች፣ በጎ ፈቃደኞችና ነዋሪዎችም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም