የገና በዓል በላሊበላ በድምቀት መከበሩ ቅርሱን ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ፋይዳው የላቀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የገና በዓል በላሊበላ በድምቀት መከበሩ ቅርሱን ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ፋይዳው የላቀ ነው
ወልዲያ፤ታኅሣስ 29/2018 (ኢዜአ)፦የገና በዓል በላሊበላ በድምቀት መከበሩ ቅርሱን ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ፋይዳው የላቀ መሆኑ ተመላከተ፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) በርካታ ምዕመናን፣ የውጭና የሀገር ውስጥ ታዳሚዎች በተገኙበት በላሊበላ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፤ መንግስት ለላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ ቅርሱ ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ህብረተሰቡም አንድነቱን በማጠናከር ለአካባቢው ዘላቂ ሰላምና ልማት መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።
ታሪካዊ ቅርሶችና እሴቶችን ከመጠበቅና ከመንከባከብ ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ትንሳኤ እውን ለማድረግ በጋራ ለልማት መትጋት ይገባልም ብለዋል።
የጥንት አያቶችን ህያው ቅርሶችና ትውፊቶች በመጠበቅና አዲስ ታሪክ በመስራት አሰባሳቢ ትርክት መገንባት ከዛሬው ትውልድ ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ፤ መንግስት ቅርሶችን ከመጠበቅና ከመንከባከብ ባለፈ አዳዲስ መዳረሻዎችን በማልማት ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በርካታ ቅርሶች በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት በማስመዝገብ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን በማስታወስ፤ የገና በዓል በላሊበላ በድምቀት መከበሩ ቅርሱን ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አራጌ ይመር፤የገና በዓል በርካቶች በታደሙበት በላሊበላ በድምቀት መከበሩን ገልጸዋል።
የገና በዓል ለሰው ልጆች ሁሉ የሠላምና የፍቅር ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው በጫካ የሚገኙ ወገኖች ከጽንፍና ጥላቻ በመውጣት የሰላምን እድል እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
በበዓሉ የተገኙት የተለያዩ ሊቀ ጳጳሳትም ኢትዮጵያ ሰላሟና አንድነቷ ጸንቶ እንዲኖር ህዝቡ አንድነት፣ ፍቅርና አብሮነቱን ማጠናከርና ለሰላሙ ተግቶ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የሰሜንና ደቡብ ወሎ እንዲሁም የከሚሴ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ ኤርምያስን ጨምሮ ሌሎች ክቡራን ሊቃነ ጳጳሳትና እንግዶች ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ እስከ ቤዛ ኩሉ ስነ ስርአት ታድመዋል።