ቀጥታ፡

ባርሴሎና ከአትሌቲኮ ቢልባኦ ለስፔን አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ፍጻሜ ለማለፍ ይጫወታሉ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 29/2018 (ኢዜአ)፦ የስፔን አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የግማሽ የፍጻሜ መርሃ ግብር ዛሬ እና ነገ በሳዑዲ አረቢያ ይካሄዳል። 

ምሽት አራት ሰዓት ባርሴሎና ከአትሌቲኮ ቢልባኦ ጋር በኪንግ አብደላ ስፖርትስ ሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። 

ባርሴሎና 15 ጊዜ ውድድሩን በማሸነፍ የክብረ ወሰኑ ባለቤት ነው። አትሌቲኮ ቢልባኦ ሶስት ጊዜ ዋንጫውን አንስቷል። 

ሁለቱ ክለቦች በስፔን የአሸናፊዎች  አሸናፊ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለዘጠነኛ ጊዜ ነው። 

ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ስምንት ጨዋታዎች ባርሴሎና አራት ጊዜ ሲያሸንፍ አትሌቲኮ ቢልባኦ ሶስት ጊዜ ድል ቀንቶታል። አንድ ጊዜ አቻ ወጥተዋል። 

ከስምንቱ ጨዋታዎች ስድስቱ የፍጻሜው ጨዋታ ደርሶ መልስ በነበረበት ወቅት የተካሄዱ ናቸው።

እ.አ.አ በ2025 በስፔን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በጅዳ ባደረጉት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ባርሴሎና በጋቪ እና ላሚን ያማል ግቦች 2 ለ 0 አሸንፏል።

እ.አ.አ በ2021 በፍጻሜው ተገናኝተው አትሌቲኮ ቢልባኦ 3 ለ 2 አሸንፏል። 

በ2025/26 የስፔን ላሊጋ ባርሴሎና በ49 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። አትሌቲኮ ቢልባኦ በ24 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል። 

የዛሬው ጨዋታ አሸናፊ ክለብ በፍጻሜው ከአትሌቲኮ ማድሪድ እና ሪያል ማድሪድ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።

የስፔን አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የተጀመረው እ.አ.አ 1982 ነው።

ውድድሩ እ.አ.አ 1982 እስከ 2019 የስፔን ላሊጋ እና የስፔን የኮፓ ዴል ሬይ (ጥሎ ማለፍ) ዋንጫ አሸናፊዎች የሚጫወቱበት ነበር።

የስፔን እግር ኳስ ማህበር እ.አ.አ በ2020 ባደረገው ማስተካከያ የስፔን የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በስፔን ላሊጋ እና በስፔን ጥሎ ማለፍ ዋንጫ በተመሳሳይ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን የያዙ ክለቦች እንዲሳተፉ ተደርጓል።

ባርሴሎና የወቅቱ የላሊጋ እና የኮፓ ዴል ሬይ አሸናፊ ሲሆን ሪያል ማድሪድ በሁለቱም ውድድሮች ላይ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

እንደዚህ አይነት ሁኔታ በሚገጥምበት ወቅት በሊጉ ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ ክለቦች እንደሚሳተፉ የውድድር ደንቡ ያስቀምጣል።

በዚሁ መሰረት አትሌቲኮ ማድሪድ እና አትሌቲኮ ቢልባኦ በዘንድሮው ውድድር ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም