ቀጥታ፡

የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ኮትዲቯር ለሩብ ፍጻሜ አለፈች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 28/2018 (ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመጨረሻ የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር ኮትዲቯር ቡርኪናፋሶን 3 ለ 0 አሸንፋለች።

ማምሻውን በማራካሽ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታው አማድ ዲያሎ በ20ኛው፣ ያን ዲዮማንዴ በ32ኛው እና ባዙማና ቱሬ በ87ኛው ደቂቃ የማሸነፊያ ጎሎቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

አማድ በውድድሩ ላይ ያስቆጠራቸውን ግቦች ብዛት ወደ ሶስት ከፍ አድርጓል።

ተጫዋቹ ከጎሉ በተጨማሪ ለዲዮማንዴ ጎል ኳሱን አመቻችቶ አቀብሏል። የጨዋታው ኮከብ ሆኖም ተመርጧል።

በጨዋታው ላይ ኮትዲቯር ብልጫ ወስዳ ተጫውታለች።

ድሉን ተከትሎ የወቅቱ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ኮትዲቯር ሩብ ፍጻሜ የገባች የመጨረሻዋ ሀገር ሆናለች።

በሩብ ፍጻሜው ከሰባት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ግብጽ ጋር የምታደረገው ጨዋታ ከወዲሁ የሚጠበቅ ነው።

ዛሬ በተደረገ ሌላኛው የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር አልጄሪያ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን 1 ለ 0 በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅላች።

ጨዋታዎቹን ተከትሎ የጥሎ ማለፍ መርሃ ግብር ተጠናቋል።

አዘጋጇ ሞሮኮ ከካሜሮን፣ ኮትዲቯር ከግብጽ ፣ ናይጄሪያ ከአልጄሪያ እና ማሊ ከሴኔጋል በሩብ ፍጻሜው ይጫወታሉ።

የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ጥር 1 እና 2 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም