ቀጥታ፡

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በዚህ ሳምንት ይጀምራል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 28/2018(ኢዜአ)፦ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በዚህ ሳምንት እንደሚጀምር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ በመረቁበት ወቅት የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በአዲሱ ዓመት ከሚጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ እንደገለጹት የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የግንባታ ማብሰሪያ መርሃ ግብር በዚህ ሳምንት ይከናወናል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአዲስ አበባ የሚገኘውን ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት ሲጠቀምበት መቆየቱን አስታውሰዋል።

የአየር መንገዱ አገልግሎት በሰፋበት ወቅት አውሮፕላን ማረፊያው የአቅሙ መጨረሻ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።


 

በዚህም ምክንያት የአየር መንገዱን አገልግሎት በብቃት የሚሸከመው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ይፋ መሆኑን ተናግረዋል።

10 ቢሊየን ዶላር ወጪ የሚደረግበት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚሸጋገርበት የግንባታ ማብሰሪያ መርሃ ግብር በዚህ ሳምንት እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም