ቀጥታ፡

የመስጠት በዓል የሆነውን ገና የተቸገሩትን በማገዝ ስጦታዎችን በመለዋወጥ እናከብራለን- የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዎች 

ሃዋሳ፤ ታህሳስ 28/2018 (ኢዜአ)፦ የገና በዓልን የተቸገሩ ሰዎችን  በማገዝና  አብሮነትን የሚያጠናክሩ ስጦታዎችን በመለዋወጥ እደሚያከብሩት የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የገና በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበር ሃይማኖታዊ በዓል ነው።

በዓሉ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ ባህላዊ እሴቶች የሚጎሉበትና ስጦታን በመለዋወጥ መልካምነት የሚገለጥበት  በመሆኑ ያላቸውን በማካፈል በዓሉን በጋራ ለማክበር መዘጋጀታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ለበዓሉ ሲሸምቱ ካነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወይዘሮ መሰረት ታምራት እና ልጃቸው ኤፍራታ ሚፍታህ የገናን በዓል ከጓደኞቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ጋር ስጦታን በመለዋወጥና ካላቸው ለተቸገሩ ወገኖች በማካፈል  በአብሮነት እንደሚያሳልፉ ተናግረዋል።

ይህም እርስ በርስ መተሳሰብና ቤተሰባዊነትን እንደሚያጠናክር ገልጸው፤ የስጦታ ልውውጥም ፍቅርን፣ መተሳሰብና አንድነት እንዲጎለብት ያደርጋል ብለዋል።

ሌላኛው የሃዋሳ ከተማ ነዋሪ አቶ ተካልኝ በቀለ በበኩላቸው የገና በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም መሰጠትን  አስተምሮ ለሰዎች ፍቅር በመስጠትና እርስ በርስ በመደጋገፍ የምናስቀጥልበት ነው ብለዋል፡፡

እሳቸውም የኢትዮጵያዊያንን የመተጋገዝ ባህልን ለትውልድ ለማውረስ ጭምር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የገናና የጥምቀት በዓላት ካላቸው ሀይማኖታዊ ስርአታ በተጓዳኝ ኢትዮጵያዊ የብዝሀ ባህል ባለቤት መሆኗንም  እንደሚያሳዩ ያነሱት ደግሞ ዲዛይነር ይመኑ ዮሐንስ ናቸው፡፡

በዓሉ በተለይ በሀገር ባህል አልባሳት ደምቆ የሚታይበትና ማህበራዊ ትስስር የሚጎለብትበት መሆኑን አንስተዋል።

በዓሉን ስጦታ በመለዋወጥ እና ያለው የሌለውን በመደገፍ በፍቅርና በአንድነት የሚያከብረው ነው ብለዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም