ቀጥታ፡

ለጋስነት ያጠናከረው ጉርብትና  

(በያንተስራ ወጋየሁ-ዲላ ኢዜአ)

በዓል ሲደርስ ሁሉም እንደ አቅሙ ቤት ባፈራው አብሮነትና ደስታ ለማክበር ሽር ጉድ ማለት አይቀሬ ነው።

በጉን፣ ዶሮውን፣ ዳቦና ጠላውን እንደ አቅሙ የቻለውን በማዘጋጀት ወዳጅ፣ ዘመድና ጎረቤት እየተጠራራ በዓልን በድምቀት ማሳለፍ የተለመደ ባህላችን ነው።

ኢትዮጵያውያን በዓል ሲመጣ በጋራ፣ በፍቅርና በአብሮነት ተሰባስበን ማሳለፍ፤ የሌላቸውን የመርዳትና የመደጋገፍ የቆየ ልምድም አለን።

ይሄ የመተሳሰብ በጎ ባህላችን እንዳለ ሆኖ በጌዴኦ ዞን የሆነውን አንድ ለየት ያለ ነገር እናውጋችሁ፤ ነገሩ የተፈጸመው በዞኑ ዲላ ዙሪያ ወረዳ ቱምትቻ ቀበሌ ነው።

ልትፈርስ በደረሰች ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ማርያም ጉዬ የተባሉ አባት ከሦስት ልጆቻቸው ጋር ይኖራሉ። ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት በጉልበት ሥራ በሚያገኙት አነስተኛ ገቢ ነው። ሦስቱም ልጆቻቸው ለአቅመ አዳምና ሄዋን አልደረሱም። ባለቤታቸውን በሞት ያጡ ከመሆናቸው ባለፈ አካል ጉዳተኛ በመሆናቸው ልጆቻቸውን በብቸኝነት ለማሳደግ ግድ ብሏቸዋል።

ልጆቻቸውን ለማኖር አካል ጉዳተኛነታቸው ሳይገድባቸው በሰዎች ማሳ በምንጣሮና በሌሎች የጉልበት ስራዎች በመሰማራት በሚያገኙት ጥቂት ገቢ ኑሯቸውን ለማሸነፍ ዘወትር ይታትራሉ።

እኝህ አባት ታዲያ በገና በዓል ዋዜማ እሳቸውን ጨምሮ ብዙዎችን ያስደሰተና ለሌሎችም ምሳሌ የሆነ አጋጣሚ ገጥሟቸዋል። 


 

"ኑሮ ካሉት ... " እንዲሉ ሆነና በጠባብና ልትፈርስ በደረሰች ደሳሳ ጎጆ ለዘመናት በችግር ውስጥ ቢያሳልፉም ዛሬ ኑሯቸው ተለውጧል።

የቤቷ ጥበትና ለመውደቅ መድረሷ የዘወትር ጭንቀታቸው ቢሆንም ተስፋ ባለመቁረጥ የኑሮ ሩጫቸውን አላቋረጡም።

በዚህ መሀል ነው እንግዲህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮና የተጠሪ ተቋማት አመራርና ሠራተኞች ወዳሉበት የመጡት።

በጌዴኦ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ለአቅመ ደካሞች ቤት በማደስና በመገንባት ድጋፍ የሚያደርጉት ተቋማቱ የአቶ ማርያም ጉዬን ቤት ለማደስ እንደመጡ ሲሰሙ ደስታቸው ወደር አልነበረውም።

ዘጠኝ ካሬ የማትሞላው ይዞታቸው ግን ሌላው ፈተና ሆነች። ተቋማቱ አዲስ መኖሪያ ቤትና መጸዳጃ ቤት ለመገንባት 100 ካሬ ቦታ ይፈልጋሉ። የእሳቸው ቦታ ግን በእጅጉ ያነሰች መሆኗ ለሰሪዎቹ ግራ የሚያጋባ ሆነ።

መቶ ካሬ ካልሞላ ቤቱ እንዴት ይገነባል በሚል ግራ በተጋቡበት ወቅት ታዲያ "ጉርብትና ለመቼ ነው እኔ እያለሁ ወንድሜ እንዴት መውደቂያ ያጣል” ያሉ አንድ ጎረቤታቸው ባልተለመደ ሁኔታ ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ተነሱ።

አቶ ከበደ ቦሮጂ ይባለሉ። የአቶ ማርያምን ተስፋ የሚያለመልም በጎነት ይዘው ከተፍ አሉ።

ከባለቤታቸውና ከዘጠኝ ልጆቻቸው ጋር የሚኖሩት አቶ ከበደ 300 ካሬ ሜትር ይዞታቸው ላይ 100 ካሬ በመቀነስ ለአቶ ማርያም እንዲሰጥና ቤቱ እንዲሰራላቸው ፈቅደው ቦታውን አስረከቡ።።

ለዘመናት የቆየው ጉርብትና ያስተሳሰራቸው ሁለቱ ወንድማማቾች ፍቅራቸውን በመተጋገዝ አሳዩና ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመጡትን ሁሉ ያስደመመ ታሪክ ሰሩ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮና የተጠሪ ተቋማት አመራርና ሠራተኞች ለወገን ደራሽ ወገን ነው በሚል እሳቤ ከአቶ ከበደ ቦርጂ በተለገሰው 100 ካሬ ቦታ ላይ ለአቶ ማርያም ጉዬ የገነቡትን መኖሪያ ቤትም ትናንት አስረክበዋል።

ስፋቷ ሶስት በሶስት ከሆነች ደሳሳ ጎጇቸው ውጭ ምንም አይነት ያልነበራቸው አቶ ማርያም በጎረቤታቸውና በተቋማቱ መልካም ፈቃድ ዛሬ የአዲስ ቤት ባለቤት ሆነዋል።

ለአካል ጉዳታቸው ሳይበገሩ ኑሯቸውን ለማቅናት በጉልበት ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ማርያም ዛሬ የገና በዓልን በአዲስ ቤት ከልጆቻቸው ጋር በደስታ ያከብራሉ።

ልትፈርስ በደረሰች ደሳሳ ጎጆ ውስጥ በባዶ ቤት ከልጆቻቸው ጋር በዓል ሊያሳልፉ የነበሩት አቶ ማርያም ዛሬ በደስታ ተውጠው በዓልን ለማሳለፍ እየተዘጋጁ ነው።

"ሳይደግስ አይጣላም" እንዲሉ ሆነና  በገና በዓል ዋዜማ ወደ ቤታቸው የገባው ደስታ መቼም የማይዘነጉትን ውለታ ጭምር ነው ያመጣላቸው።

ካላቸው መሬት ቆርጠው የሰጡት ጎረቤታቸው አቶ ከበደ ካለኝ 300 ካሬ የመኖሪያ ይዞታ ውጭ ሃብት ንብረት የለኝም። ይሁንና ጎረቤቴ እድሉ ከሚያመልጠው ካለኝ ባካፍለው ተያይዘን ማደግ እንችላለን በሚል በጎ ተግባሩን እንደፈጸሙና በዓሉን በአብሮነት ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በገና ዋዜማ ቤቱ ተመርቆ በማየታቸውም ደስታቸውን እጥፍ ድርብ አድርጎታል። በጎነት ለሌሎች ደስታ ለመፍጠር ካለን የምናካፍልበት ሰናይ ተግባር መሆኑን በመረዳት ሁሌም ለተቸገሩ እንድረስ ሲሉም ይገልጻሉ።

አቶ ማርያም ቤቱን ሲረከቡ ሲቃ እየተናነቃቸው ድጋፍ ላደረጉላቸው አካላት ምስጋና አቅርበዋል።  ቤታቸው በአዲስ መልክ መገንባቱ ቀሪ ህይወታቸውን በደስታ እንዲኖሩ የሚያስችል ነው። አቶ ከበደ ጎረቤት ብቻ ሳይሆኑ ወላጅ አባቴ ጭምር ናቸው ሲሉም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


 

በጎነት ከመልካም ህሊና የሚመነጭ ሰናይ ተግባር እንደሆነና ሁሉም ይህን አይነት በጎ ተግባር በመፈጸም ወገኑን ማገዝ እንዳለበት የገለጹት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ መሪሁን ፍቅሩ(ዶ/ር) ናቸው።

ለአቶ ማርያም የተደረገው በጎ ተግባር ለብዙዎች አርዓያ ይሆናል። የተቸገረን መርዳት፣ ያጣን ማገዝ የኢትዮጵያውያን ባህላችን ቢሆንም ዛሬ መሬት ቆርሶ በመስጠት የተቸገረን መርዳት ከጉርብትናም በላይ ነውና ለሁላችንም ትምህርትን የሚሰጥ ነው። ይህም ከአቶ ማርያም ይልቅ ለጋሹ አቶ ከበደ ምንኛ ውስጣዊ ደስታ እንደሚሰማቸው መገመት አይከብድም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም