በወልቂጤ ከተማ ከ250 ለሚበልጡ አቅም የሌላቸው ወገኖች የበዓል መዋያ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በወልቂጤ ከተማ ከ250 ለሚበልጡ አቅም የሌላቸው ወገኖች የበዓል መዋያ ድጋፍ ተደረገ
ወልቂጤ፤ ታህሳስ 28/2018(ኢዜአ)፦ በውልቂጤ ከተማ አስተዳደር የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ከ250 ለሚበልጡ አቅም የሌላቸው ወገኖች የበዓል መዋያ ድጋፍ ተደረገ።
ድጋፍ የተደረገላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም የተደረገላቸው ድጋፍ በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ ሙራድ ከድር በዚህ ወቅት እንደገለጹት ድጋፉ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት፤ በየአካባቢው ያሉ ወጣቶች እና የእምነት ተቋማትን በማስተባበር የተደረገ ነው።
በዚህም በተለያየ መክንያት ለችግር የተዳረጉ ከ250 በላይ ዜጎች ለገና በዓል መዋያ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።
በዓል በሚከበርበት ወቅት ኢትዮጵያዊ የመረዳዳትና የመተሳሰብ እሴቶቻችን በማስቀጠል አብሮነታችንን ማጠናከር አለብን ሲሉም ገልጸዋል።
በተደረገው የበዓል መዋያ ድጋፍ ለአረጋውያንና አቅመ ደካማ ወገኖች ቅድሚያ መሰጠቱን ጠቅሰው፣ ለድጋፉ ከ400 ሺህ ብር በላይ ወጪ መደረጉን ተናግረዋል።
ወይዘሮ ይስሬሸ ኸሊል በዓል በመጣ ቁጥር ማጣታቸው ያስጨንቃቸው እንደነበር አስታውሰው፣ ዛሬ የተደረገላቸው ድጋፍ በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል፡፡
የበዓል መዋያ ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ሌላው የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ትዕግስት ጋሻው ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ አካላትን በማስተባበር በበአል ወቅት ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የተለያዩ አካላትን በማስተባበር ዶሮ፣ እንቁላል፣ ዘይት እና የዳቦ ዱቄት ማሰባሰባቸውን የተናገሩት ደግሞ ታደሰ ለማ ናቸው።