ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ከተሞች በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት፣ በንግድ እና በገቢ አሰባሰብ ዘርፍ አበረታች እድገት እድገት እየተመዘገበ ነው

ባህርዳር፤ ታህሳስ 28/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ከተሞች በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት፣ በንግድ እና በገቢ አሰባሰብ ዘርፍ አበረታች እድገት እየተመዘገበ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የክልሉ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አሕመዲን ሙሐመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ክላስተር አስተባባሪ የሚመራ የክላስተሩ ቢሮዎች እና ተቋማት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተካሂዷል።


 

የዘርፉ አስተባባሪ አህመዲን መሀመድ(ዶ/ር) እንደገለጹት የክልሉን የ25 ዓመት አሻጋሪ የልማት ዕቅድ መሰረት ያደረገ አደረጃጀት በመፍጠር የክላስተሩ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ እየተሰራ ነው።

ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት፣ በንግድ እና በገቢ አሰባሰብ ዘርፎች አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።

የከተማ የኢኮኖሚ ዘርፉ መነቃቃትም ለህዝቡ ምርትና አገልግሎትን በጥራት እንዲሁም በስፋት ማቅረብ እንዳስቻለ ተናግረዋል።


 

የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው የክልሉን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም የኢንዱስትሪ ዘርፍ የልማት አቅምን የበለጠ ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ከ182 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ከ1ሺህ 800 በላይ አልሚ ባለሃብቶች የንግድ ፈቃድ መስጠት መቻሉን ገልጸዋል።

አሰራርን በማዘመንና የአገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፍ የክልሉን ኢንዱስትሪ የመልማት ዕምቅ አቅም በአግባቡ ለመጠቀም የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።


 

የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም ሙሀመድ(ዶ/ር) በበኩላቸው ባለፉት ስድስት ወራት ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚውል አንድ ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል የግብርና ምርት ማቅረብ ተችሏል።

ይህም የዘይት ፋብሪካዎችን ጨምሮ ሌሎች አምራች ኢንዱስትሪዎች በአቅማቸው ልክ እንዲያመርቱ ማድረጉን ጠቁመው ግብዓት የማቅረብ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

ከዚህ ጋር በማያያዝም በምርቶች ላይ ባዕድ ነገር በመቀላቀል ለገበያ ለማቅረብ በሚሞክሩ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እና ነዳጅን በህገ ወጥ መንገድ በሚከዝኑ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱንም ተናግረዋል።

ምርትን በመደበቅና ያለምንም ምክንያት የዋጋ ንረትን ሲያባብሱ በነበሩ 800 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እንደተወሰደም ነው ያስታወቁት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም